በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ዩክሬን በሞስኮ ላይ የድሮን ጥቃት መፈፀሟን ሩሲያ አስታወቀች


ዩክሬን በሞስኮ ላይ የድሮን ጥቃት መፈፀሟን ሩሲያ አስታወቀች
ዩክሬን በሞስኮ ላይ የድሮን ጥቃት መፈፀሟን ሩሲያ አስታወቀች

የሩሲያ አየር መቃወሚያዎች፣ ሞስኮን ኢላማ ያደረጉ በርካታ የዩክሬን ሰው አልባ አውሮፕላኖችን (ድሮኖችን) መትተው ማክሸፋቸውን እና አንድ ድሮን ግን በዋና ከተማው የሚገኝ ሰማይ ጠቀስ ህንፃ መትቶ ማፈራረሱን ባለስልጣናት ማክሰኞ እለት አስታወቁ።

የሞስኮ ከንቲባ ሰርጌ ሶብያኒን በቴሌግራም በኩል ባስተላለፉት መልዕክት፣ ጥቃት የደረሰበት ህንፃ፣ እሁድ እለት በሌላ የዩክሬን የድሮን ጥቃት ተመትቶ የነበረ መሆኑን አመልክተዋል። በማክሰኞው ጥቃት ምንም አይነት ጉዳት ስለመድረሱ አልተገለፀም።

የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር ዛሬ ባወጣው መግለጫ፣ ሰራዊቱ፣ በጥቁር ባህር ላይ የሚገኙ የሩሲያ የጥበቃ መርከቦች ላይ ያነጣጠሩ ሶስት የዩክሬን ባህር ሰርጓጅ ድሮኖችን ማክሸፋቸውን አስታውቋል። ጥቃቱ የተፈፀመው ከሩሲያ በደቡብ ምዕራብ ከሚገኘው ሴቫስቶፖል ከተማ በ340 ኪሎሜትር ርቀት ላይ መሆኑንም ሩሲያ አመልክታለች።

በሌላ በኩል ሩሲያ በደቡብ ዩክሬን በሚገኘው ኬርሰን ከተማ ባካሄደችው የቦምብ ጥቃት አንድ ዶክተር መገደሉን እና አንድ ነርስ መቁሰሏን ባለስልጣናት አስታውቀዋል። በካርኪቭ ቀጠናም፣ ሩሲያ ኢራን ሰራሽ በሆኑ ድሮኖች አካሄደች በተባለ ጥቃት አንድ የትምህርት ተቋም እና አንድ የስፖርት ማዕከል የሚገኝበት ህንፃ ላይ ጉዳት ማድረሱን፣ የአካባቢው ባለስልጣናት ገልፀዋል።

ሩሲያ በዩክሬን ከተሞቹ ላይ ባካሄደችው ጥቃት የደረሰውን ጉዳት ተከትሎ፣ የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮለድሚር ዘለንስኪ፣ ዩክሬን ረጅም ርቀት የጦር መሳሪያዎች እንደሚያስፈጓት አፅንዖት ሰጥተው ተናግረዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት ባለሥልጣናት፣ ዩክሬንን በሚመለከት በሳዑዲ አረብያ በሚካሄድ ጉባዔ ላይ እንደሚገኙ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ ማቲው ሚለር ትናንት ሰኞ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አመልክተዋል። በመጪው ሳምንት በጅዳ ይካሄዳል ተብሎ በሚጠበቀው ጉባዔ፣ ሩሲያ በዩክሬን ላይ የምታካሂደውን ጦርነት ለማስቆም ዘለንስኪ ያቀረቡት የሰላም እቅድ ላይ ውይይት ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG