· ኤኮዋስ መፈንቅለ መንግሥቱን አወገዘ
የኒዤር ወታደራዊ መኰንኖች፣ ጀኔራል አብዱራህማኔ ቺያኔን፣ ዛሬ ዐርብ፣ ዐዲስ ርእሰ ብሔር አድርገው ሠይመዋል፡፡
መኰንኖቹ፣ ፕሬዚዳንት መሐመድ ባዙምን፣ በመፈንቅለ መንግሥት ከሥልጣን ካወረዱ በኋላ፣ ሕገ መንግሥቱንና የቀድሞ መንግሥታዊ ተቋማትን ማስወገዳቸውን አስታውቀዋል፡፡
ጀነራል ቺያኔ፣ ከትላንት በስቲያ ረቡዕ፣ ብልሹ አስተዳደር እና የደኅንነት ችግር በመባባሱ ምክንያት፣ የቀድሞውን ፕሬዚዳንት ከሥልጣናቸው በማስወገድ የፕሬዚዳንቱን መኖሪያ ቤት እና ጽ/ቤት የተቆጣጠረው፣ የፕሬዚዳንቱ ልዩ ጠባቂ ዘብ አዛዥ እንደኾኑ ተነግሯል፡፡
ዛሬ ዐርብ፣ በቴሌቪዥን መስኮት ብቅ ብለው በታዩት ጀነራል ምስል ሥር፣ “ዐዲስ የተቋቋመው ወታደራዊ ምክር ቤት እና የአገር ጠባቂ ብሔራዊ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት” የሚል ተጽፎ መታየቱ ተመልክቷል፡፡
በሌላ በኩል፣ የምዕራብ አፍሪካ ሀገራት የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ(ECOWAS)፣ በኒዤር የተካሔደውን ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት አወግዟል።
በልዩ ዘባቸው ቁጥጥር ሥር የዋሉት ፕሬዚዳንት መሐመድ ባዙም፣ በአስቸኳይ እንዲለቅቁ፣ ኤኮዋስ መጠየቁን፣ የቪኦኤው ጄምስ በቲ ዘግቧል።
በሌላ በኩል፣ አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ እንደዘገበው፣ በመፈንቅለ መንግሥት መሪዎቹ ቁጥጥር ሥር ያሉትን ፕሬዚዳንት ባዙምን፣ የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ዒማኑኤል ማክሮን፣ ዛሬ ማለዳ አነጋግረዋቸዋል።
በኮሎኔል አማዱ አብድራማኔ የተመሩት ፕሬዚዳንታዊ የክብር ዘብ መኰንኖች፣ ፕሬዚዳንቱን በቁጥጥር ሥር አውለው የመንግሥቱን ሥልጣን መቆጣጠራቸውን፣ ከትላንት በስተያ ረቡዕ ዐውጀዋል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዥ፣ “በዴሞክራሲያዊ መንገድ በተመረጠ መንግሥት ላይ የተፈጸመ ጥቃት ነው፤” ሲሉ፣ የመፈንቅለ መንግሥቱን ድርጊቱን አውግዘዋል።
የቪኦኤው ጄምስ በቲ ያነጋገራቸው የኤኮዋስ የፖለቲካ እና የጸጥታ ጉዳዮች ኮሚሽነር አብደል ፋቱ ሙሳ፣ የኒዤር ሕጋዊ መሪ ፕሬዚዳንት ባዙም፣ በአፋጣኝ ወደ ሥልጣን እንዲመለሱ እንጠይቃለን፤ ብለዋል።
“በክልላችን ዴሞክራሲን ለማጠናከር የያዝነውን ርምጃ፣ አብዝቶ ወደ ኋላ የሚጎትት ከባድ አድራጎት ነው፤” ያሉት ኮሚሽነሩ፣ “እንደምታውቀው ሦስቱም የማእከላዊ ሣህል ሀገራት፣ የሽብር ጥቃት ውስጥ ናቸው፤” ብለዋል፡፡
ኮሚሽነሩ አያይዘውም፣ “በሦስቱም በዴሞክራሲያዊ መንገድ በተመረጡ መንግሥታት ላይ፣ መፈንቅለ መንግሥት ተካሒዷል። ኤኮዋስ፣ ይህ መፈንቅለ መንግሥት እንዳይሳካ ቆርጦ ተነሥቷል፤” ሲሉ አክለዋል፡፡
መድረክ / ፎረም