የዳን ክሎዚንግ ብራንድ መሥራች እና ዲዛይነር የኾነችው ወጣቷ ዳናዊት ዓለማ፣ ወደ ዲዛይኒንግ የጥበብ ዘርፍ ከተቀላቀለች ሦስት ዓመት አስቆጥራለች፡፡ በርግጥ፣ ወደ ጥበቡ ዓለም መሳብ የጀመረችው በልጅነቷ ነው፡፡ “ፍላጎቱ ከልጅነቴ ጀምሮ የነበረ ነው፤” ትላለች፡፡ ለውስጠ ቤት የተለያዩ ጌጣጌጦችን፣ ለአሻንጉሊቶቿ ደግሞ አልባሳትን እየሠራች ማደጓንም ታወሳለች፡፡ ከልጅነቷ ጀምሮ የምትወደውን ይህን ጥበብ፣ በሒደት በትምህርት እና ሥልጠና በማዳበርም፣ የፋሽን ዲዛይነር ለመኾን በቅታለች፡፡
ዳናዊት፣ በፋሽን ዲዛይን ሥራዎቿ፥ በቅድ፣ በስፌት እና በዐይነት ለየት ያሉ አልባሳትን ትሠራለች፡፡ ብዙ ጊዜ እንደሚታየው፣ ለበዓላት እና ለልዩ ልዩ ፕሮግራሞች ሳይኾን፣ በአዘቦት ቀን የሚለበሱ ልብሶችን ዲዛይን ታደርጋለች፡፡
“ሙሉ በሙሉ በኢትየጵያ የሚመረቱ ጨርቆችን ነው የምጠቀመው፤” የምትለው ዳናዊት፣ በበዓላት እና በተለያዩ ፕሮግራሞች የሚለበሱ ባህላዊ አልባሳት በሚገባ እንደተሠራባቸው እና ኢትዮጵያን በሚገባ እያስተዋወቁ እንዳሉ ትገልጻለች፡፡ በኢትዮጵያ ጨርቆች እየተሠሩ በማንኛውም ቀን ሊለበሱ የሚችሉ ባህላዊ አልባሳትን ማግኘት አዳጋች መኾኑ ትኩረቷን እንደሳበው ትናገራች፡፡ በመኾኑም፣ ፍላጎቷ፥ በአዘቦት ቀን የሚለበሱ አልባሳትን ወደ መሥራቱ ማድላቱን ታመለክታለች፡፡
ዳናዊት፣ “የፋሽን ሥራዎቼ ታሪክ ነጋሪዎች ናቸው፤” ትላለች፡፡ በአልባሳት ሥራዎቿ፣ ለየት ያሉ ታሪኮችን መግለጽ እንዳለባትም ታምናለች፡፡ ሰዎች የፋሽን ሥራዎቿን ሲለብሷቸው፣ የአንድ ታሪክ አካል እንደኾኑ እንዲሰማቸውም ትሻለች፡፡ ኾኖም፣ በሰው ዘንድ ተቀባይነትን ማግኘት፣ ልዩ ዐይነት የፋሽን ሥራን እንደ መከተሏ ቀላል አልነበረም፡፡ በጥበብ ሥራዋ ከባዱ ነገር፣ “መሥራት የምትፈልገውንና በገበያው የሚያዋጣውን ነገር ማጣጣም መቻል ነው፤” ትላለች ዳናዊት፡፡ “ገበያውን ብቻ ተከትለኽ ስትሠራ፣ የፈጠራ ችሎታኽን ታጣለኽ፡፡ ውስጥኽን ብቻ እያዳመጥኽ ስትሠራ ደግሞ፣ የንግድ ሥራው ይዳከማል፤” ስትል ታስረዳለች፡፡ ዳናዊት በዘርፉ ስለምታደርገው እንቅስቃሴ እና ልምድ አጋርታናለች።
ሙሉውን ከተያያዘው ፋይል ይከታተሉ።
መድረክ / ፎረም