በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የሱዳን ግጭት የጤና ስርዓቱን እያወደመ ነው ሲል ተመድ አስታወቀ


ፋይል - የሱዳን ስደተኞች ቻድ በሚገኘው ዛቦት የስደተኞች መጠለያ ውስጥ
ፋይል - የሱዳን ስደተኞች ቻድ በሚገኘው ዛቦት የስደተኞች መጠለያ ውስጥ

በሱዳን የሚካሄደው ውጊያ የሀገሪቱን ደካማ የጤና ስርዓት ለአጠቃላይ ውድቀት እየዳረገው በመሆኑ፣ በሚሊየን የሚቆጠሩ ሱዳናውያን ለድንገተኛ ወይም ሥር የሰደደ የጤና እክሎች ህክምና ማግኘት አይችሉም ሲል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ትላንት አስታውቋል።

የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብዓዊ ድጋፍ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ (ኦቻ) ባወጣው መግለጫ ግጭት፣ የአቅርቦት እጥረት፣ በህክምና ተቋማት ላይ የደረሰው ጉዳት ወይም በቁጥጥር ስር መሆን፣ እንዲሁም በህክምና ሰራተኞች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች፣ በሰዎች ህይወት እና የጤና አገልግሎት የማግኘት ችሎታ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሱ ነው ብሏል።

የዓለም ጤና ድርጅትም በበኩሉ እስካሁን በጤና አገልግሎት ተቋማት ላይ በተፈፀሙ 50 የሚደርሱ ጥቃቶች ለ10 ሰዎች መሞት እና 21 ሰዎች መቁሰል ምክንያት ሆነዋል ብሏል።

የዓለም ጤና ድርጅት የምስራቅ ሜዲትራኒያን አካባቢ ቢሮ የአደጋ ጊዜ ዳይሬክተር ሪክ ብሬናን፣ ካይሮ ከሚገኘው ቢሮዋቸው እንደተናገሩት፣ የሱዳን ግጭት የሳምባ ምች፣ ተቅማጥ፣ የአይምሮ ጤና አገልግሎት እና የፅንስ እንክብካቤን ጨምሮ፣ በጣም መሰረታዊ የሆኑ የጤና አገልግሎት ተደራሽነት ላይ ከፍተኛ ተፅእኖ አሳድሯል። ብሬናን አክለው እንደ የስኳር በሽታ እና የደምግፊት ያሉ ሥር የሰደደ ህመም ያለባቸው ሰዎችም ህክምና እንዳያገኙ አግዷቸዋል ብለዋል።

የዓለም ጤና ድርጅት ባወጣው መረጃ መሰረት በአሁኑ ሰዓት ሱዳን ውስጥ 11 ሚሊየን ሰዎች አስቸኳይ የጤና እርዳታ ቢያስፈልጋቸውም አገልግሎት እየሰጡ ያሉት ጥቂት የህክምና ተቋማት ብቻ ናቸው። ሁለት ሶስተኛው ወይም ሰማኒያ ከመቶ የሚሆኑት ሆስፒታሎች አገልግሎት እየሰጡ አይደለም ያሉት ብሬናን፣ በምዕራብ ዳርፉር አንድ ሆስፒታል ብቻ በከፊል እየሰራ መሆኑንም ጨምረው ጠቁመዋል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG