በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በሱዳን ግጭት ከሦስት ሚሊዮን በላይ ሰዎች እንደተፈናቀሉ ተመድ አስታወቀ


የሱዳን ተፈናቃዮች በቻድ
የሱዳን ተፈናቃዮች በቻድ

በሱዳን በመባባስ ላይ ባለው ግጭት ሳቢያ፣ ወደ ጎረቤት አገሮች የሸሹትን ከ700 ሺሕ በላይ ሰዎችን ጨምሮ፣ 3ነጥብ1 ሚሊዮን ሰዎች እንደተፈናቀሉ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዛሬ ሲያስታውቅ፣ ግጭቱ ሙሉ ለሙሉ ወደለየለት የእርስ በእርስ ጦርነት እንዳያመራ ስጋቱ አይሏል።

ግጭቱ፣ ባለፈው ሚያዝያ ሰባት ቀን ከጀመረበት ጊዜ አንሥቶ፣ ከሦስት ሺሕ በላይ ሰዎች ሕይወታቸውን ሲያጡ፣ ከስድስት ሺሕ በላይ ደግሞ እንደቆሰሉ፣ የአገሪቱ ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።

2ነጥብ4 ሚሊዮን የሚደርሱ ሰዎች በሀገር ውስጥ እንደተፈናቀሉ፣ ዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት(IOM) አስታውቋል።

ወደ ጎረቤት ሀገራት ከሸሹት ውስጥ፣ ግብጽ፥ ከ255 ሺሕ በላይ በመቀበል ከፍተኛውን ቁጥር ስታስተናግድ፣ ኢትዮጵያም እስከ አሁን ከ62 ሺሕ በላይ እንደተቀበለች ታውቋል።

አራት የቀንዱ ሀገራት በአባልነት የታቀፉበት ኢጋድ(የምሥራቅ አፍሪቃ የልማት በይነ መንግሥታት ባለሥልጣን) መሪዎች እና ተወካዮች፣ ከትላንት በስቲያ ሰኞ፣ በሱዳን ጉዳይ ላይ ለመነጋገር፣ ዐዲስ አበባ ውስጥ ተሰብስበው፣ ጦርነቱ በአስቸኳይ እንዲቆም የአቋም መግለጫ አውጥተው ነበር።

የሱዳን መንግሥት በኢጋድ ቡድን የወጣውንና ‘ሰላም ለማስከበር የውጪ ሀገራት ወታደሮች በአገሪቱ እንዲሠማሩ’ የሚለውን የጋራ መግለጫ ተቃውሟል። በተጨማሪም፣ በኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የቀረበውንና በሱዳን ሰማይ ላይ በረራ እንዲከለከል የሚጠይቀውን ሐሳብ፣ የሱዳን መንግሥት መቃወሙን፣ የአሶሺዬትድ ፕረስ ዘገባ አመልክቷል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ የእንግሊዝ መንግሥት፥ ከተፋላሚ ኃይሎቹ ጋራ ግንኙነት አላቸው ባላቸው ስድስት የንግድ ተቋማት ላይ ማዕቀብ መጣሉን አስታውቋል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG