በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በቤንሻንጉል ጉምዝ ሲቪሎች በታጣቂዎች መገደላቸውን ነዋሪዎች ገለፁ


በቤንሻንጉል ጉምዝ ሲቪሎች በታጣቂዎች መገደላቸውን ነዋሪዎች ገለፁ
please wait

No media source currently available

0:00 0:05:29 0:00

በቤንሻንጉል ጉምዝ ሲቪሎች በታጣቂዎች መገደላቸውን ነዋሪዎች ገለፁ

በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል መተከል ዞን ግልገል በለስ ከተማ፣ ባለፈው ሳምንት ዐርብ፣ በታጣቂዎች በተከፈተ ተኩስ፣ ሲቪሎች መገደላቸውን ነዋሪዎች ተናገሩ።

የከተማው ነዋሪዎች ለአሜሪካ ድምፅ እንደተናገሩት፣ በዕለቱ ከቀኑ 10:30 ጀምሮ፣ በተለምዶ ቻይና ካምፕ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ፣ ታጣቂዎች በከፈቱት ተኩስ፣ 10 የሚደርሱ ሰላማውያን ሰዎች ሲገደሉ፣ ከዘጠኝ በላይ የሚኾኑቱ ደግሞ ቆስለው በሕክምና ላይ ይገኛሉ፡፡

ግድያውን የፈጸሙት፣ በጫካ የነበሩና በቅርቡ እርቀ ሰላም ፈጽመው ከገቡ የ“ጉሕዴን ተመላሾች” ውስጥ ትጥቅ ያልፈቱ ኀይሎች እንደኾኑ፣ ያመለከቱት ነዋሪዎቹ፣ ካለፈው ሳምንት ቅዳሜ ጀምሮ፣ ወደ አጎራባች ከተማ ፓዌ እየተሰደዱ እንደኾነም አክለው ገልጸዋል፡፡

የጉምዝ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ሊቀ መንበር አቶ ግራኝ ጉደታ፣ በሰሞኑ ጥቃት እጃቸው አለበት ስለተባሉ የጉምዝ ታጣቂዎች፣ ከመንግሥት ጋራ ኾነው በማጣራት ላይ እንዳሉና ሲጠናቀቅም መግለጫ እንደሚሰጡ ለአሜሪካ ድምፅ ተናግረዋል፡፡ ከክልሉ መንግሥት ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ለጊዜው አልተሳካም፡፡

ስማቸውን እንዳንጠቅስ የጠየቁን የግልገል በለስ ከተማ ነዋሪ፣ በዕለቱ ከቀኑ 10:30 ገደማ ጀምሮ፣ ታጣቂዎቹ፣ በተለይ 01 እና 02 ቀበሌ ተኩስ በመክፈት፣ በመልክ እየለዩ እንደገደሉ እና እንዳቆሰሉ ተናግረዋል፡፡

“ስሜን አልጠቅስም” ያሉን ሌላው አስተያየት ሰጪም፣ ታጣቂዎቹ፣ ከቻግኒ ወደ ፓዌ በርካታ ሰዎችን ይዞ እየተጓዘ የነበረን ተሽከርካሪ አስገድደው በማስቆም፣ በውስጡ በነበሩ ተሳፋሪዎች ላይም ተኩስ መክፈታቸውን ገልጸዋል፡፡

በጉዳዩ ላይ መልስ እንዲሰጡን፣ በእጅ ስልካቸው ላይ ደውለን የጠየቅናቸው፣ የቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ሐሩን ዑመር፣ ቀጠሮ ካስያዙን በኋላ በሰዓቱ መልሰን ብንደውልም ለጥሪው ባለመመለሳቸው፣ አስተያየታቸውን ለማካተት አልቻልንም፡፡

ነዋሪዎቹ ለጥቃቱ ተጠያቂ ያደረጉት፣ በቅርቡ ከክልሉ መንግሥት ጋራ እርቀ ሰላም ፈጽመው የገቡ፣ በአሁኑ ሰዓት ካምፕ ውስጥ የሚኖሩና ትጥቅ ያልፈቱ የ“ጉዴን ተመላሽ” ታጣቂዎች ናቸው፤ ብለዋል፡፡

የጉምዝ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ሊቀ መንበር አቶ ግራኝ ጉደታ ግን፣ ይህን ውንጀላ አይቀበሉም፡፡ በአሁኑ ሰዓት ታጣቂዎቻቸው፥ ወደ ሰላማዊ ሕይወት ተመልሰው፣ በመንግሥት መዋቅር እና በሌሎች ልዩ ልዩ የሞያ ዘርፎች ተሠማርተው እንደሚገኙ፣ ሊቀ መንበሩ ለአሜሪካ ድምፅ ተናግረዋል፡፡

የጥቃቱ ሰለባዎች እንደሚሉት፣ ካለፈው ቅዳሜ ጠዋት ጀምሮ፣ የግልገል በለስ ከተማ ነዋሪዎች፣ ወደ አጎራባች ከተማ ፓዌ እየሄዱ ነው፡፡ ስማቸውን ያልጠቀሱት ሁለቱ አስተያየት ሰጪዎች፣ ቤተሰቦቻቸውን በፓዌ ከተማ አስቀምጠው፣ ንብረታቸውን ለመጠበቅ ወደ ግልገል በለስ ከተማ እንደተመለሱ አክለው ገልጸዋል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን ወደ ሥልጣን መምጣት ተከትሎ፣ በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል ልዩ ልዩ አካባቢዎች፣ ማንነትን መሠረት ባደረገ ተደጋጋሚ ጥቃት፣ በርካቶች መገደላቸውንና መቁሰላቸውን መዘገባችን ይታወቃል፡፡

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG