በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የሱዳን ተፋላሚ ወገኖች በአስቸኳይ ተኩስ እንዲያቆሙ ኢጋድ ጠየቀ


ፋይል - የሱዳን ጦር ወታደሮች ካርቱም ውስጥ ሞተር ብስክሌት ሲነዱ
ፋይል - የሱዳን ጦር ወታደሮች ካርቱም ውስጥ ሞተር ብስክሌት ሲነዱ

አራት አባላት ያሉት የልማት በይነ መንግስታት ባለሥልጣን፣ በምጻሩ ኢጋድ ቡድን፣ በሱዳን በመካሄድ ላይ ባለው ግጭት ላይ ለመነጋገር አዲስ አበባ ላይ ዛሬ ስብሰባ አካሂዶ የአቋም መግለጫ አውጥቷል።

ቡድኑ ባወጣው የአቋም መግለጫ በሱዳን ያለውን ችግር ወታደራዊ እርምጃ እንደማይፈታው እና የቡድኑ ጥረትም የሁለቱን ተፋላሚ ወገኖች መሪዎችን ፊት ለፊት በማገናኘት ላይ የሚያተኩር እንደሚሆን አስታውቋል።

የኢጋድ ቡድኑ በተጨማሪም ሁለቱ ወገኖች በአስቸኳይ እና ካለ ምንም ቅድመ ሁኔታ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲፈርሙ፣ የስምምነቱን ተግባራዊነትን በተመለከተም ቁጥጥር የሚደረግበት መንገድ እንዲበጅ ጥሪ አድርጓል።

የምሥራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ኃይልን በተመለከተ ጉባኤ እንዲደረግ እንደሚጠይቅና ሲቪሎችን ለመከላከል እና ሰብዓዊ ተደራሽነትን ለማረጋገጥ ኃይሉ እንዲሠማራ እንደሚሻም የቡድኑ የአቋም መግለጫ አመልክቷል።

በመላ ሱዳን የተንሰራፋው አስከፊ የሰብዓዊ መብት ረገጣ በተለይም ሴቶችን እና ልጃገረዶችን ኢላማ ያደረገው የጾታ ጥቃት እንዳስዳሰበው እና እንደሚያወግዝ እንዲሁም የመብት ጥሰት ፈጻሚዎችንም ለፍርድ ለማቅረብ እንደሚሠራ የኢጋድ ቡድኑ አስታውቋል።

በሱዳን ያሉ ሁሉም ወገኞች የሚሳተፉበት እንዲሁም በሱዳናውያን የሚመራ እና ባለቤት የሆኑበት ሁሉን አቀፍ ንግግር እንዲጀመር ጥሪ ያደረገው ቡድኑ፣ ኢጋድ እና የአፍሪካ ኅብረት በቅርቡ ሂደቱን እንደሚጀምሩ ይፋ አድርጓል።

ለአንድ ቀን በአዲስ አበባ የተደረገው ጉባኤ በኬንያው ፕሬዝደንት ዊሊያም ሩቶ የተመራ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ፣ ጂቡቲ እና ደቡብ ሱዳን መሪዎች እና ተወካዮች ተሳታፊ ሆነውበታል። በተጨማሪም የአውሮፓ ኅብረት፣ ግብጽ፣ ሳዑዲ አረቢያ፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ፣ አሜሪካ እና እንግሊዝ ተወካዮች እንደተገኙበት የአቋም መግለጫው አስታውቋል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG