በጀርመን ጊሰን ከተማ በተካሔደው አወዛጋቢ የኤርትራ ሙዚቃ ዐውደ ትርኢት(ፌስቲቫል) ላይ በተነሣ አለመረጋጋት፣ ከ20 በሚበልጡ የፖሊስ አባላት ላይ ጉዳት ሲደርስ፣ ግርግሩን ለማስቆም ፖሊስ አስለቃሽ ጋዝ እና የውኃ ቅንቡላ ተኩሷል።
የአካባቢው ፖሊስ በትዊተር ገጹ እንዳስታወቀው፣ በወቅቱ በየወገኑ በተሰለፉ ኤርትራውያን “በተወረወሩ ድንጋዮች”፣ በ26 የፖሊስ አባላት ላይ ጉዳት ሲደርስ፣ ወደ 100 የሚጠጉ ሰዎች መታሰራቸውን ገልጿል።
እስከ እሑድ ድረስ ይካሔድ በነበረው ዐውደ ትርኢት ላይ፣ ከ2ሺሕ እስከ 3ሺሕ ሰዎች ይሳተፋሉ ተብሎ ተጠብቆ ነበር።
የፌስቲቫሉ አዘጋጆች፣ ምስጢራዊ በኾነ የአንድ ፓርቲ ዓምባገነን አገዛዝ ሥር ከምትገኘው የኤርትራ መንግሥት ባለሥልጣናት ጋራ ቅርበት አላቸው በሚል ክሥ ይቀርብባቸዋል።
የሄስ ክልል የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ፒተር ቤውዝ፣ “እንዲህ ዐይነቱ፣ በመከላከያ ኃይላችን ላይ ያነጣጠረ የኃይል ተግባር፣ በጭራሽ ተቀባይነት የለውም፤” ብለዋል። የጀርመን መንግሥት፣ የኤርትራ አምባሳደርን እንዲጠራና “የኤርትራ አለመግባባቶች” በጀርመን ምድር ላይ መከሠት እንደሌለባቸው በግልጽ እንዲያሳውቋቸውም ጥሪ አቅርበዋል።
በቀይ ባሕር ዳርቻ የምትገኘውና ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የተገለለችው ሀገር፣ በቅርቡ በሰሜን ኢትዮጵያ በተካሔደው ጦርነት፣ ሠራዊቷ በትግራይ ክልል ያደረሰውን የመብት ጥሰት ጨምሮ፣ በቀጣናው ግጭቶች ጣልቃ በመግባቷ ማዕቀብ ተጥሎባታል።
ኤርትራ በግንቦት ወር 1991 ዓ.ም. ከኢትዮጵያ ተገንጥላ፣ ግንቦት 24 ቀን 1993 ነፃነቷን በይፋ ያወጀች ሲኾን፣ በጨቋኝ አገዛዛቸው በሚታወቁት ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈ ወርቂ እየተመራች ትገኛለች።
መድረክ / ፎረም