በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ክለስተር ቦምብ ለዩክሬን በመላክ ጉዳይ ላይ ባይደን እና ሱናክ ልዩነት አላቸው


የብሪታንያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሪሺ ሱናክ ከዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ጋር በለንደን ተገናኝተዋል። ሐምሌ 10፣ 2023
የብሪታንያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሪሺ ሱናክ ከዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ጋር በለንደን ተገናኝተዋል። ሐምሌ 10፣ 2023

በሊትዌንያ በሚካሄደው የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ ወደዛው በማቅናት ላይ የነበሩት የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝደንት ጆ ባይደን እግረ መንገዳቸውን እንግሊዝ ጎራ ብለዋል።

የእንግሊዙ ጠቅላይ ሚኒስትር ሪሺ ሱናክ ፕሬዝደንት ባይደንን በቢሯቸው ተቀብለው ማነጋገራቸው ሲታወቅ፣ እንግሊዝን ጨምሮ በ123 አገሮች የተከለከለውን ክለስተር ቦምብ የባይደን አስተዳደር ለዩክሬን እንደሚልክ ሰሞኑን ማስታወቁ በሁለቱ አገራት መካከል ልዩነትን ፈጥሯል ተብሏል። ፈንጂው ሰዎችን በጅምላ ይገድላል በሚል አገራት ጥቅም ላይ እንዳይውል አግደው ነበር። ሱናክ የባይደን አስተዳደርን ሃሳብ በይፋ አልደገፉም። “እንግሊዝ የክለስተር ፈንጂዎችን ምርት እና ጥቅም ላይ መዋልን የሚከለክለው ዓለም አቀፍ ስምምነት ፈራሚ ነች፣ ጥቅም ላይ መዋሉንም አታበረታታም” ሲሉ ሱናክ ባለፈው ቅዳሜ ተናግረው ነበር።

ሁለቱ መሪዎች ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ ለ6ኛ ግዜ መገናኘታቸው ነው።

የክለስተር ቦምብ የመላክ ውሳኔው በኔቶ ውስጥ ክፍፍል ይፈጥር እንደሁ የተጠየቁት የዋይት ሃውስ ብሔራዊ አማካሪ ጄክ ሰለቨን፣ “ሱናክ በዓለም አቀፍ ስምምነቱ መሠረት ሕጋዊ ግዴታቸውን እየተወጡ ነው” ሲሉ መናገራቸውን የቪኦኤዋ ዋይት ሃውስ ዘጋቢ ፓትሲ ዊዳኩስዋራ ሪፖርት አመልክቷል።

ባይደን ከሱናክ ጋር የነበራቸውን ስብሰባ እንዳጠናቀቁ ወደ ዊንሰር ካስል በማቅናት ከንጉስ ቻርለስ ጋር ተገናኝተዋል።

ዛሬ ይጀመራል ተብሎ የሚጠበቀው የኔቶ ጉባኤ፣ በዋናነት በዩክሬን ጉዳይ ላይ የሚያተኩር ሲሆን፣ የቃል ኪዳን ድርጅቱ በሚስፋፋበት ጉዳይ ላይም ይመክራል ተብሏል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG