ስዊድንን የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት ወይም በምጻረ ቃሉ ‘ኔቶ’ ዓባል ለማድረግ የሚደረገው ጥረት ቀጥሎ፣ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅቱ ዋና ጸሃፊ ጀንስ ስቶልተንበርግ ከቱርክ፣ ስዊድን እና ፊንላንድ ከከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር ዛሬ ይወያያሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የስቶልተንበርግ ጥረት የመጣው የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝደንት ጆ ባይደን፣ ከስዊድኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ኦልፍ ክርስተርሰን ጋር ከተገናኙ በኋላ እና፣ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅቱ ጉባኤውን በሚቀጥለው ሳምንት ሊቱዌኒያ ላይ ከማድረጉ በፊት፣ ቱርክ የሰዊድንን አባልነት እንድታጸድቅ ለማግባባት ዋይት ሃውስ ጥረት በሚያደርግበት ወቅት ነው።
ስዊድን የጦር ቃል ኪዳን ድርጅቱን ይበልጥ እንደምታጠናክረው ባይደን ትናንት ለስዊድኑ ክርስተርሰን ተናግረዋል።
“ዩናይትድ ስቴት የሰዊድንን የኔቶ ዓባልነት ሙሉ ለሙሉ ትደግፋለች፣ ስዊድን ቃል ኪዳኑን ታጠናክረዋለች” ብለዋል ባይደን።
ፊንላንድ ባለፈው ሚያዚያ ኔቶን የተቀላቀለች ሲሆን፣ የስዊድን ጉዳይ ግን፣ ቱርክ እና ሃጋሪ ስምምነታቸውን ባለመግለጻቸው ተስተጓጉሎ ቆይቶል።
የቃል ኪዳን ድርጅቱ አዲስ ዓባል ለመሆን፣ ነባር ዓባላቱ ሁሉ በአንድ ድምጽ መስማማት አለባቸው።