ዩናይትድ ስቴትስ፣ በዛሬው ዕለት፣ የኑክሌር መሣሪያ መሸከም የሚችሉ ቦምብ ጣይ አውሮፕላኖችን፣ በደቡብ ኮሪያ እና ሰሜን ኮሪያ አካባቢ ማብረሯ ታውቋል። በረራው፣ በሰሜን ኮሪያ መዲና ፒዮንግያንግ፣ ፀረ አሜሪካ ሰልፍ ከተካሔደ ከቀናት በኋላ እንደተደረገና ወታደራዊ ጡንቻዋን ለሰሜን ኮርያ ለማሳየት የታለመበት እንደኾነ፣ የአሶሺዬትድ ፕረስ ዘገባ አመልክቷል።
የረጅም ርቀት ተኳሽ ቦምብ ጣይ ቢ-52 አውሮፕላኖቹ፣ ከሌሎች የአሜሪካ እና የደቡብ ኮሪያ ተዋጊ ጄቶች ጋራ በአንድነት፣ ወታደራዊ ልምምድ ማድረጋቸውን፣ የደቡብ ኮሪያ መከላከያ ሚኒስቴር አስታውቋል።
የኑክሌር ተሸካሚ ቦምብ ጣይ አውሮፕላኖቹ በአካባቢው መታየታቸው፣ ሰሜን ኮሪያ፥ የኑክሌር ዐቅሟን በማፈርጠም ላይ ባለችበት በዚኽ ወቅት፣ በአጸፌታው ለደቡብ ኮሪያ የሚቀርቡ ስልታዊ መሣሪያዎችን ማሳያ እንደኾነም ተጠቁሟል። የአሜሪካንን ስልታዊ እና ወታደራዊ ዐቅም እንደሚያጠናክርም፣ የደቡብ ኮሪያው የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።
ዩናይትድ ስቴትስ፣ ከሁለት ሳምንታት በፊት፣ 150 ታማሃክ ሚሳየሎችን መሸከም የሚችል ኑክሌር ተሸካሚ ሰርጓጅ መርከብ፣ ወደ ደቡብ ኮሪያ የባሕር ክልል ልካለች፡፡ ሰርጓጅ መርከቧ በአካባቢው የተከሠተችው፣ ሰሜን ኮሪያ የሚሳየል ሙከራዋን በላይ በላዩ መደጋገሟን ተከትሎ ነው።