በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በሱዳን ጾታዊ ጥቃት እየተስፋፋ እንደሆነ ተመድ ገለጸ


በሱዳን ጾታዊ ጥቃት እየተስፋፋ እንደሆነ ተመድ ገለጸ
please wait

No media source currently available

0:00 0:03:17 0:00

በሱዳን ጾታዊ ጥቃት እየተስፋፋ እንደሆነ ተመድ ገለጸ

በሱዳን ምዕራብ ዳርፉር እየተካሔደ ያለው ግጭት እና ሁከት፣ በሴቶች ላይ ጾታዊ ጥቃት እንዲባባስ አድርጓል፤ ሲል፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስታወቀ።

ወደ ጎረቤት ቻድ ከሸሹት ብዙዎቹ እንደሚሉት፣ በሱዳን፣ የሕግ እና ሥርዐት መፍረስ፣ በሴቶች ላይ የሚደርሰው ጥቃት እንዲጨምር አድርጓል።

ቪኦኤ ማንነቷ እንዳይታወቅ ስሟን የማይጠቅሳት ሴት፣ በዳርፉር ግጭቱ ሲጀምር፣ የትውልድ መንደሯን ጥላ ሸሽታለች፡፡ በአብዛኛው አረብ የኾኑትና ጃንጃዊድ የተሰኙ፣ ጥቁር ሱዳናውያንን ዒላማ የሚያደርጉ ታጣቂዎች፣ ከእህቷ ጋራ ተደብቃ ከነበረችበት ቤቷ ገብተው፣ ሁለቱንም እንደደፈሯቸው፣ ሴቲቱ ተናግራለች፡፡

ሙና ማሊክ፣ በዳርፉር የጾታ እኩልነት አቀንቃኝ ናቸው፡፡ በሱዳን፣ በጎሣዎችም መካከል ግጭት እንዲፈጠር መንሥኤ የኾነው፣ የሁለቱ ጄኔራሎች ትጥቃዊ ግጭት ከጀመረ አንሥቶ፣ የተፈጸሙ ጾታዊ መደፈሮችን፣ ሙና ማሊክ በመሰነድ ላይ ናቸው፡፡

“በርካታ ሲቪሎች ተገድለዋል። ወንዶች፣ ሴቶች፣ ልጆችም ጭምር በአንድ ላይ። የግል እና የሕዝብ ንብረቶች ተዘርፈዋል። ሕንጻዎችንም አቃጥለዋል። በዚኽ መሀከልም፣ አንዳንድ ሴቶች እና ልጃገረዶች ተደፍረዋል፤” ሲሉ፣ ሙና ማሊክ ለቪኦኤ ተናግረዋል።

የጾታ እኩልነት አቀንቃኟ እንደሚሉት፣ እስከ አሁን 11 መደፈሮችን መዝግበዋል። ይህ ግን፣ገና ጅምሩ ይመስላል።

በሱዳኑ ግጭት፣ የጾታ ጥቃት፣ በተለይም መደፈር እንደተፈጸመ መሰማቱ እጅግ እንዳሳሰበው፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ይገልጻል።

ግጭቱ ከጀመረ ወዲህ፣ መርማሪዎች እና ጋዜጠኞች ወደ ሱዳን ዘልቀው መግባት ባለመቻላቸው፣ የወንጀሉን መጠን ለማወቅ አስቸጋሪ ኾኗል።

የችግሩን መጠን ማወቁ እጅግ አስፈላጊ ነው፤ ምክንያቱም፣ በተናጠል የተፈጸመ መደፈር፣ በተለምዶ የወንጀል ፍ/ቤት ሲታይ፣ ኾን ተብሎ በዘመቻ መልክ የሚፈጸም መደፈር ግን፣ እንደ ጦር ወንጀል ስለሚቆጠር፣ በዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት የሚታይ ጉዳይ ነው። ይህም ማለት፣ የየትኛውም ቡድን መሪዎች ቢኾኑ፣ ኾን ተብሎ በተቀነባበረ ኹኔታ ለተፈጸመ መደፈር ተጠያቂ ይኾናሉ።

“በተመድ በመደረግ ላይ ያለው ማጣራት፣ ጥቃቱ በምን ዓይነት መንገድ እንደተፈጸመ፣ ኹኔታውን ለማወቅ ይረዳል። በካርቱምም ኾነ በዳርፉር እየተባባሰ እንደኾነ ለማወቅ ተችሏል፤” ብለዋል፣ ኾን ተብሎ በተቀነባበረ መንገድ መደፈር ተፈጽሞ እንደሁ በቪኦኤ የተጠየቁት፣ በተመድ የሴቶች ጉዳይ ምክትል ሓላፊ ሣራ ደግለስ።

በሱዳን፣ የጤና ባለሞያዎች መደፈር ስለመኖሩ፣ ደግለስ ተናግረዋል። በጦርነቱ መሀከል ተጠምደው የነበሩ ሴቶችም፣ ስጋት እንደሚሰማቸው በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴ ሲገልጹ ተስተውለዋል። ለሰለባዎቹ፣ ማኅበራዊ አገልግሎት ባለመኖሩ እና መገለልን በመፍራት፣ ሰለባዎቹ፥ መደፈራቸውን ባለመናገራቸው ምክንያት፣ በርካታ መደፈሮች ሪፖርት ሳይደረጉ ይቀራሉ።

በቻድ የተመድ የሕዝብ ፕሮግራም ምክትል ተወካይ ኤሊስ ካካም፣ በቅርቡ፣ 10 የተደፈሩ ሴቶችን፣ ከቻድ ጋራ በሚያዋስነው ድንበር ላይ እንዳገኟቸው ተናግረዋል።

“ዐዲስ ከደረሱት ውስጥ፣ ሴቶቹ ነፍሰ ጡሮች ናቸው። በአማካይ ከ15 እስከ 17 ዕድሜ ላይ ናቸው። ከባለቤታቸው ጋራ መኾናቸውን ለማወቅ ሞክሬ ነበር፤ ግን፣ አንዳቸውም ባል እንዳላቸው አልነገሩኝም። ስለዚኽ፣ እነዚኽ ሴት ልጆች፣ ለጊዜው በርግጠኝነት ለይተን ያላወቅነው አንዳች ዐይነት ችግር ሰለባ

ናቸው፤ ማለት ነው። ሴቶቹ መደፈር ደርሶባቸው ከኾነ፣ ሰው እንዲያውቅ አይፈልጉም፤” ብለዋል ኤሊስ ካካም።

በቪኦኤ ቃለ መጠይቅ የተደረገላትና በመግቢያው ላይ የተጠቀሰችው ሰለባ፣ አሁን እህቷ፣ ነፍሰ ጡር እንደኾነች ተናግራለች፡፡

እንግዱ ወልዴ ወደ አማርኛ መልሶታል፡፡

XS
SM
MD
LG