የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን የትጥቅ አመጽ የሀገር ክህደት መሆኑን እና በሀገራቸው ላይ መሳሪያ የሚነሳ ማንኛውም ሰው ቅጣት እንደሚጠብቀው በመጠቆም የዋግነር ቅጥር ተዋጊዎችን በዛሬው ዕለት አስጠንቅቀዋል።
ፑቲን በድንገተኛው የቴሌቭዥን ስርጭት ንግግራቸው ፣ የዋግነር አዛዥ ይቪግኒ ፕሪጎዢን ኃይሎቻቸው በቁጥጥር ስር እንዳደረጓት የተናገሩላትን በደቡባዊ ሩሲያ የምትገኘውን ሮስቶቭ-ኦን-ዶን ከተማን ለማረጋጋት ወሳኝ እርምጃ እንደሚወስዱ ቃል ገብተዋል።
"ይህ ለሩሲያም ሆነ ለህዝባችን ትልቅ ጥፋት ነው።አባት ሀገራችንን ከእንዲህ ዓይነቱ ስጋት ለመከላከል የምንወስደው እርምጃ ከባድ ይሆናል። ሆን ብለው በክህደት ጎዳና ያመሩ፣ የትጥቅ ዓመፅን ያስተባበሩ፣የዛቻ መንገድን እና የሽብርተኝነት ዘዴዎች የመረጡ ሁሉ አይቀሬ ቅጣት ይቀጣሉ ። ለህግ እና ለህዝባችንም ምላሽ ይሰጣሉ " ሲሉ የተናገሩት ፑቲን፣ የዋግነር ቡድንን ድርጊት "ከጀርባ ሆኖ መውጋት " ሲሉ ጠርተውታል።
ፕሪጎዢን የሩሲያን ጦር አመራር ለማስወገድ ከዛቱ በኃላ ፣ ሀገሪቱ የጸረ-ሽብርተኝነት ዘመቻ በሞስኮ እንዲነቃነቅ ማድረጓን ዛሬ ማለዳ አስታውቃለች ።ሩሲያ ቅጥር ተዋጊዎቹ ከወጋነር ቡድን እና መሪ ጋር እንዲለያዩ ጥሪ አቅርባለች
ፕሪጎዢን በሮስቶቭ የሚገኘውን የሩሲያን ጦር ዋና መስሪያ ቤት ኃይሎቻቸው እንደተቆጣጠሩ እና የከተማዋ የጦር ጣቢያዎች በተዋጊዎች እጅ ስር እንዳሉ ተናግረዋል ።
ዋይት ሀውስ በሩሲያ ከፍተኛ ወታደራዊ ባለስልጣናት እና በዋግነር ሃይል መካከል ያለውን ፍጥጫ እየተከታተለ መሆኑን እና በሚከሰቱ ለውጦች ዙሪያ ከአጋሮች ጋር እንደሚመክር የብሄራዊ ደህንነት ምክር ቤት ቃል አቀባይ አደም ሆጅ አርብ ዕለት ለቪኦኤ ተናግረዋል ።
የብሪታንያ ባለስልጣናት ቅዳሜ ቅዳሜ በሩሲያ ያለውን ሁኔታ እየተከታተሉ መሆናቸውን ተናግረዋል ። "በሚቀጥሉት ሰዓታት ውስጥ የሩሲያ የጸጥታ ሃይሎች ታማኝነት በተለይም የሩሲያ ብሄራዊ ጥበቃ ጓድ አቋም ቀውሱ ወዴት እንደሚያመራ ለማወቅ ቁልፍ ጉዳይ ነው። ይህ በቅርብ ጊዜ ውስጥ የሩሲያን መንግስት የገጠመውን ትልቅ ፈተናን ይወክላል" ሲል የብሪታንያ የመከላከያ ሚኒስቴር በቲውተር ገጹ ላይ አስፍሯል ።
የዋግነር ቡድን መሪ ፕሪጎዢን አርብ እንዳስታወቁት የዋግነር የመስክ ጦር ጣቢያዎች በሮኬቶች፣ በሄሊኮፕተር ተተኳሾች እና በመድፍ የሩሲያ ጦር አዛዥ በሆኑት ጄኔራል ቫለሪ ገራሲሞቭ ትዕዛዝ ተደብድበዋል። ጌራሲሞቭ ትዕዛዙን የሰጠው ከመከላከያ ሚኒስትሩ ሰርጌይ ሾይጉ ጋር ከተገናኙ እና ዋግነርን ለማጥፋት ከወሰኑ በኋላ ነው በማለት ከሰዋል ።
የሩሲያ የመከላከያ ሚኒስትር ክሱን ውድቅ አድርጓል ።