ነገ፤ ቅዳሜ፣ ወደ 2ሺ የሚገመቱ ከሰሃራ በታች ካሉ የአፍሪካ አገሮች የተነሱ ፍልሰተኞች ከሞሮኮ ወደ ስፔይን ለመሻገር ያደረጉት ሞት ያስከተለ ሙከራ የሚታወስበት ቀን ነው፡፡ በዚህ ሙከራ ቢያንስ 37 ሰዎች ሲሞቱ 76 የሚሆኑት እስካሁን የደረሱበት አልታወቀም፡፡
አምነስቲ ኢንተርናሽናል ሞሮኮና ስፔይ በድንበር ላይ በአፍሪካውያን ፍልስተኞች ላይ የሚፈጸሙትን የዘረኝነት ተግባራቸውን ይሸፋፍናሉ ሲል ዛሬ ዓርብ ከሷል፡፡
የስፔይን ዐቃቤ ህጎች በስፔይን ጸጥታ ኃይሎች የተፈጸመ ምንም ዓይነት የወንጀል ጥፋት አላገኘንም በሚል ምርመራውን ካቋረጡ በኋላ፣ ስፔይን ገለልተኛ ምርመራ አላደረገችም ያለው አምነስቲ፣ ሞሮኮም ምንም አይነት ምርመራ አላደረገችም ብሏል፡፡
አምነስቲ በመግለጫው “በሁለቱ አገራት ትብብር የተነሳ፣ የሞሮኮ ባለስልጣናት፣ ከሰሃራ በታች ያሉ ጥቁር አፍሪካውያን፣ በሞሮኮ ድንበር በኩል ወደ ስፔይን ግዛት በመድረስ፣ የፖለቲካ ጥገኝነት እንዳይጠይቁ መከልከላቸውን ቀጥለዋል” ብሏል፡፡
22 አስክሬኖች እሁንም በሞሮኮ አስክሬን ማቆያ ውስጥ እንደሚገኙ አምነስቲ አስታውቋል፡፡