የዩናይትድ ስቴትስ፣ ላለፉት አምስት ዐሥርት ዓመታት ያህል የዘለቀውንና ከሦስት ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ስደተኞችን በመቀበል ሕይወታቸውን የታደገችበትን የደግነት ባህሏን በማዘመን፣ አሜሪካኖች፥ በግል ስደተኞችን የሚቀበሉበት ዐዲስ ፕሮግራም፣ በዚህ ዓመት ተግባራዊ ማድረጓን፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን አስታወቁ፡፡
ትላንት የተከበረውን፣ “የዓለም ስደተኞች ቀን” በማስመልከት፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ባወጡት መግለጫ እንዳስታወቁት፣ “በሚደረግባቸው ጫና እና ግፊት ምክንያት፣ አገራቸውን ጥለው በሌሎች አገሮች የሚገኙ፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ስደተኞች ለሚያሳዩት፣ ፈተናን የመቋቋም ጽናት እና ከችግር መልሶ የመውጣት ብቃት፣ እንዲሁም ተቀባይ ማኅበረሰቦች ለሚያሳዩት ደግነት እና ዓለም ለሰጣቸው ምላሽ፣ እንዲሁም ሰብአዊ አጋሮቻቸው ለሰጧቸው ድጋፍ፣ እውቅና እንሰጣለን፤” ብለዋል።
ዩናይትድ ስቴትስ፣ እ.አ.አ ከ1975 ዓ.ም. ጀምሮ፣ 3ነጥብ5 ሚሊዮን ስደተኞችን ተቀብላ በቋሚነት ማሥፈሯን የጠቀሱት ብሊንከን፣ ይህ ሲወርድ ሲወራረድ የመጣ የደግነት ባህል፣ ሕይወትን የሚታደግ እና በመላ አሜሪካ ላለው ማኅበራዊ ትስስር፣ አዎንታዊ አስተዋፅኦ ያደረገ ነው፤ ብለዋል።
በአሜሪካም ይሁን በዓለም ያሉ ስደተኞች፥ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ እና ማኅበራዊ አስተዋፅኦ እንዳላቸው በታሪክ ታይቷል፤ ያሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፣ አገራቸው ለዚህ አስተዋፅኦ ተገቢውን እውቅና በመስጠት፣ የስደተኞች ቅበላ ፕሮግራሟን በማዘመን ላይ እንደምትገኝ አስታውቀዋል።
አሜሪካኖች፥ በግል ስደተኞችን የሚቀበሉበት ዐዲስ ፕሮግራም፣ በዚህ ዓመት ተግባራዊ መደረጉንም ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
ስደተኞች፣ በተስፋ እና በክብር እንዲኖሩ፣ አሜሪካ ከሌሎች ወገኖች ጋራ የምታደርገውን ትብብር እንደምትቀጥልም፣ ብሊንከን አረጋግጠዋል።