በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የስደት ሁኔታዎች እና የጥበቃ መብቶች


የስደት ሁኔታዎች እና የጥበቃ መብቶች
please wait

No media source currently available

0:00 0:04:35 0:00

የስደት ሁኔታዎች እና የጥበቃ መብቶች

በየዓመቱ እ.አ.አ ሰኔ 20 ቀን ታስቦ የሚውለው “የዓለም የስደተኞች ቀን”፣ በዓለም ዙሪያ ስደተኞች ስላሉበት ሁኔታ ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ የሚሠራበት ነው፡፡ የመጀመሪያው የዓለም የስደተኞች ቀን እ.አ.አ በ2001 ሲታሰብ፣ የ1951ዱን፣ “ከስደተኞች ጋራ የተያያዙ ጉዳዮች ኮንቬንሽን” 50ኛ ዓመት መታሰቢያ በማክበር ነበር፡፡

የ1951ዱ የስደተኞች ጉዳይ ስምምነት፣ “ስደተኛ” ማለት ምን ማለት እንደኾን በይኗል፡፡ ጥገኝነት የሚሰጣቸው ግለሰቦች፣ የሚገቧቸውን መብቶች እና ጥገኝነት ሰጪዎቹ ሀገራት ያሉባቸውን ሓላፊነቶች ዘርዝሯል፡፡

ስደተኛ

እ.አ.አ በ1951 በተፈረመው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ስምምነት መሠረት፣ ስደተኛ ማለት፣ ከሀገሩ፥ በዘሩ፣ በሃይማኖቱ፣ በትውልድ ቦታው፣ በአባልነት በሚሳተፍበት ማኅበራዊ ቡድን ወይም በፖለቲካ አመለካከቱ ምክንያት በሚሰማው የመሳደድ ስጋት የተነሣ፣ ሀገሩን ጥሎ የሚሰደድ ግለሰብ ማለት ነው፡፡

እንደ የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር (UNHCR) አኀዛዊ ትንበያ፣ እ.አ.አ በዘንድሮ 2023፣ 117ነጥብ2 ሚሊዮን ሰዎች፣ ከቀዬአቸው ይፈናቀላሉ ወይም ሀገር አልባ ይኾናሉ፡፡

ጥገኝነት ፈላጊ

ጥገኝነት ፈላጊዎች፣ በመሠረቱ ስደተኞች ሲኾኑ፣ ማመልከቻቸው ተገምግሞ ገና ሕጋዊ የስደተኛነት ዕውቅና ያልተሰጣቸው ናቸው፡፡ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር መረጃ እንደሚያሳየው፣ እአአ እስከ ሰኔ ወር 2023 ድረስ፣ በዓለም ዙሪያ የጥገኝነት ማመልከቻ አስገብተው፣ ውሳኔ እስከሚሰጣቸው የሚጠባበቁ ሰዎች ቁጥር፣ ወደ 5ነጥብ6 ሚሊዮን ደርሷል፡፡

የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች

የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች፣ መኖሪያቸውን ጥለው ተሰድደው ነገር ግን፣ መጠለያ ፍለጋ ድንበር ተሻግረው ወደ ሌላ ሀገር ያልሔዱ ሰዎች ናቸው፡፡ ምንም እንኳን፣ እነርሱም ከስደተኞቹ ጋራ ተመሳሳይ በኾኑ ምክንያቶች(የትጥቅ ግጭቶች፣ አጠቃላይ ሁከት እና የሰብአዊ መብቶች ጥሰት) የተነሣ ከቀዬአቸው ቢሰደዱም፣ በአገራቸው መንግሥት ሕጋዊ ጥበቃ ሥር ናቸው፡፡

በተመድ የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር መረጃ፣ እስከ ሰኔ ወር 2023 ድረስ፣ በዓለም ዙሪያ ያለው የተፈናቃዮች ቁጥር 61ነጥብ 2 ሚሊዮን ደርሷል፡፡

ፍልሰተኛ

የመሳደድ እና የሞት አደጋ በቀጥታ ተደቅኖባቸው ሳይኾን፣ በተለያዩ ምክንያቶች፣ የወትሮ መኖሪያቸውን ለቅቀው የሚሔዱ ሰዎች በአጠቃላይ፣ ፍልሰተኛ ተብለው ይጠራሉ፡፡

ፍልሰተኞች፣ መኖሪያቸውን ትተው የሚሔዱት፣ በጊዜያዊነት ወይም በቋሚነት፣ በሕጋዊ ወይም በሕገ ወጥ መንገድ ሊኾን ይችላል፡፡

ስደተኛ፣ የአገር ውስጥ ተፈናቃይ፣ ጥገኝነት ጠያቂ እና ፍልሰተኛ፣ ተመሳሳይ ቢመስሉም፣ የሚሰጣቸው የጥበቃ ደረጃ ይለያያል፡፡ ለምሳሌ፡- እ.አ.አ በ1951 በተፈረመው ስምምነት፣ ስደተኞች ተብለው የተፈረጁ ሰዎች የሚጠበቁላቸው፣ ነገር ግን ፍልሰተኞችን የማይጨምሩ አንዳንድ መብቶች አሉ፡፡

መንግሥታት፣ ስደተኞችን ከአገራቸው ሊያስወጡ ወይም ለሕይወታቸው አስጊ ሊኾኑ ወደሚችሉ ቦታዎች ሊመልሷቸው አይችሉም፡፡ የተጠለሉበት ሀገር፣ ለስደተኞች ማኅበራዊ አገልግሎቶችን መስጠት እና ከዐዲሱ አገራቸው ኅብረተሰብ ጋራም እንዲዋሐዱ ማድረግ አለበት፡፡

በሌላ በኩል ፍልሰተኞች፣ የሀገሩ የኢምግሬሽን ሕግ እና አሠራር ተገዢ ናቸው፡፡ ሕጉ፥ እንዳይገቡ ሊከለከላቸው፣ ከገቡም በኋላ ሊያባርራቸው ወይም ወደ አገራቸው መልሶ ሊልካቸው ይችላል፡፡

XS
SM
MD
LG