በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ናይጄሪያ ወንዝ ውስጥ በሰጠመ ጀልባ ከ100 በላይ ሰዎች ሞቱ


የናይጀሪያ ካርታ
የናይጀሪያ ካርታ

በሰሜን ማዕከላዊ ናይጄሪያ፣ ከሠርግ በመመለስ ላይ የነበሩ የቤተሰብ አባላትን የጫነች ጀልባ ሰጥማ፣ ከ100 የሚበልጡ ሰዎች መሞታቸውን፣ ፖሊስ እና የአካባቢው ባለሥልጣናት አስታውቀዋል፡፡

ክዋራ በተባለው የናይጄሪያ ግዛት ውስጥ ስለደረሰው አደጋ፣ ዝርዝር ኹኔታውን የተመለከቱ ሪፖርቶች፣ አሁንም መውጣታቸውን ቀጥለዋል፡፡

ይኹን እንጂ፣ በጀልባዎች ላይ ሰዎችን ከመጠን በላይ በመጫን ሳቢያ የሚደርሰው አደጋ የተለመደ በኾነባት ናይጄሪያ፣ የአሁኑ፥ ከእስከ ዛሬዎቹ የቅርብ ጊዜ አሳዛኝ አደጋዎች አንዱ እንደኾነ ተነግሯል፡፡

እስከ አሁን፣ 103 ሰዎች ሲሞቱ፣ ከ100 በላይ የሚኾኑቱን ከጀልባው አደጋ ለማትረፍ እንደተቻለ፣ የኩዋራ ግዛት ፖሊስ ቃል አቀባይ ኦካሳንሚ አጃዪ፣ ለአዣንስ ፍራንስ ፕሬስ ተናግረዋል፡፡ ቀሪዎቹን ፍለጋ፣ አሁንም መቀጠሉንና የአደጋው ሰለባዎች ቁጥር ከዚኽም በላይ ሊኾን እንደሚችል ተነግሯል፡፡

ባለፈው ወር፣ በሶኮቶ ግዛት በደረሰው ተመሳሳይ አደጋ፣ ከመጠን በላይ የተጫነ ጀልባ በመስጠሙ፣ ለዕንጨት ለቀማ የወጡ 15 ሕፃናት ሰጥመው ሲሞቱ፣ ወደ 25 የሚደርሱት ሌሎች ደግሞ፣ የገቡበት አለመታወቁ ተመልክቷል፡፡

ከአንድ ዓመት ቀደም ብሎ በተከሠተ አደጋ፣ 19 ሕፃናት፥ በዚያው ተመሳሳይ ወንዝ ውስጥ ሰጥመው መሞታቸው ተዘግቧል፡፡

XS
SM
MD
LG