በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በግሪክ አቅራቢያ በሰጠመ መርከብ በርካታ ፍልሰተኞች ሞቱ


በግሪክ አቅራቢያ በሰጠመ መርከብ በርካታ ፍልሰተኞች ሞቱ
please wait

No media source currently available

0:00 0:01:34 0:00

በግሪክ አቅራቢያ በሰጠመ መርከብ በርካታ ፍልሰተኞች ሞቱ

በርካታ ፍልሰተኞችን፣ ዛሬ ረቡዕ ጠዋት ጭኖ ይጓዝ የነበረ መርከብ፣ በግሪክ አቅራቢያ ተገልብጦ፣ በውስጡ የነበሩ ቢያንስ 59 ሰዎች መስመጣቸውንና የደረሱበት የማይታወቁ ተሳፋሪዎችም መኖራቸውን፣ የግሪክ የባሕር ጠረፍ ጥበቃ አስታወቀ።

በዚኽ ዓመት ከደረሱ አስከፊ የባሕር ላይ አደጋዎች አንዱ እንደኾነ በተገለጸው የመርከብ መገልበጥ አደጋ፣ 104 ሰዎች ከመስጠም ቢተርፉም፣ የመርከቡ ተሳፋሪዎች አጠቃላይ ቁጥር እስከ አሁን አልታወቀም።

ከአደጋው የተረፉ ፍልሰተኞች፣ በሌላ መርከብ፣ በግሪክ ወደምትገኘው ካላማታ ከተማ ሲወሰዱ፣ በዚያው የሚገኙ የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች፣ ወዲያውኑ የሕክምና ርዳታ አድርገውላቸዋል።

የአገሪቱ የባሕር ጠረፍ ጥበቃ እንዳስታወቀው፣ ወደ ጣሊያን በመጓዝ ላይ የነበረችው መርከብ፣ ፎሮንቴክስ በተሰኘው የአውሮፓ ኅብረት የድንበር ተቋም እና ከደቡባዊ ግሪክ በ80 ኪሎሜትር ርቀት ላይ በነበሩ ሁለት መርከቦች እይታ ውስጥ የገባችው፣ ትላንት ማክሰኞ ነበር።

ኾኖም፣ የመርከቡ ተሳፋሪዎች፥ የግሪክ ባለሥልጣናት ያቀረቡትን ርዳታ አለመቀበላቸውን ያስታወቀው የጥበቃ ቡድን፣ ከጥቂት ሰዓት በኋላ መርከቡ ተገልብጦ በመስጠሙ፣ ፈልጎ የመታደግ ሥራ መጀመሩን አስታውቋል።

አብዛኞቹ ተሳፋሪዎች፣ በ20ዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኙ ወንዶች እንደኾኑ ቢገለጽም፣ ዜግነታቸውም ኾነ መነሻቸው ከየት እንደኾነ፣ እስከ አሁን በግሪክ ባለሥልጣናት አልተረጋገጠም።

ግሪክ፥ ከመካከለኛው ምሥራቅ፣ እስያ እና አፍሪካ አህጉር ተነሥተው ወደ አውሮፓ ኅብረት ለሚጓዙ ፍልሰተኞች፣ ዋና መተላለፊያ መንገድ ስትኾን፣ በዚኽ ዓመት ብቻ፣ 72 ሺሕ የሚደርሱ ስደተኞች እና ፍልሰተኞች፣ በአውሮፓ ግንባር ቀደም መዳረሻ ወደኾኑት፥ ጣሊያን፣ ስፔን፣ ግሪክ፣ ማልታ እና ቆጵሮስ እንደገቡ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መረጃ ያመለክታል።

XS
SM
MD
LG