በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የአየር ኃይል ሓላፊው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦርድ ሊቀ መንበር ሆነው ተሾሙ


 ሌተናል ጀነራል ይልማ መርዳሳ
ሌተናል ጀነራል ይልማ መርዳሳ

የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዋና አዣዥ ሌተናል ጀነራል ይልማ መርዳሳ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ አየር መንገድ ቦርድ ሊቀ መንበር ሆነው መሾማቸውን፣ አየር መንገዱ አስታወቀ።

አየር መንገዱ ባወጣው መግለጫ፣ ሌተናል ጀነራል ይልማ፣ የአየር ኃይል አዛዥ በነበሩበት ወቅት፣ የአየር መንገዱ ቦርድ አባል ሆነው፣ ለሁለት ዓመት ከግማሽ ማገልገላቸውን ገልጿል።

ሌተናል ጀነራል ይልማ፣ በቦታው የተሾሙት፣ ለረጅም ዓመታት በአየር መንገዱ የሠሩትንና ለሁለት ዓመት ተኩል በቦርድ ሊቀ መንበርነት የመሩትን፣ የ79 ዓመት ዕድሜ ባለጸጋ፣ አቶ ግርማ ዋቄን በመተካት ነው።

አቶ ግርማ፣ አየር መንገዱ ጠንካራ እድገት ባስመዘገበበት፣ እ.አ.አ ከ2004 እስከ 2011 ባለው ጊዜም፣ የተቋሙ ዋና ሥራ አስኪያጅ ኾነው ሲያገለግሉ፣ “ለአየር መንገዱ ቡድን እድገት እና ስኬት ያበረከቱት አስተዋፅኦ፣ ትልቅ እና በአየር መንገዱ ታሪክ ውስጥ ልዩ ቦታ የሚይዝ ነው፤” ሲል፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ በመግለጫው ክብር ሰጥቷቸዋል።

ሙሉ ለሙሉ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ንብረት የኾነውና የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ መለዮው ኩራቱ እንደኾነ የሚነገረው የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ በአፍሪካ ብቸኛው ትርፋማ አየር መንገድ በመኾኑ፣ ዐቅሙንና መዳረሻዎቹን ለማጠናከር እና ለማስፋፋት የሚሠራ ሲኾን፣ እ.አ.አ. ከ2021 እስከ 2022 ባለው በጀት ዓመት፣ 937 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ትርፍ አስመዝግቧል።

XS
SM
MD
LG