በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የትረምፕን ክሥ በተመለከተ የሚደረገው ክርክር በፓርቲ ወገንተኝነት ተሟሙቋል


የትረምፕን ክሥ በተመለከተ የሚደረገው ክርክር በፓርቲ ወገንተኝነት ተሟሙቋል
please wait

No media source currently available

0:00 0:03:05 0:00

የትረምፕን ክሥ በተመለከተ የሚደረገው ክርክር በፓርቲ ወገንተኝነት ተሟሙቋል

የቀድሞው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትረምፕ፣ ኋይት ሐውስን ለቀው ሲወጡ፣ “ከፍተኛ ምሥጢራዊ የመንግሥት ሰነዶችንም ይዘው በመውጣት፣ በግል መኖሪያ ቤታቸው አስቀምጠዋል፤” በሚል የሚቀርብባቸውን ክሥ፣ ነገ ማክሰኞ፣ የፌዴራል ፍርድ ቤት በይፋ ያሰማል። በጉዳዩ ላይ፣ በአብዛኛው የፓርቲ ወገንተኝነት የሚታይበት ክርክር እየተደረገ ይገኛል፡፡

ዶናልድ ትረምፕ፣ ፍሎሪዳ በሚገኘው የፌዴራሉ ፍርድ ቤት፣ ነገ ማክሰኞ ቀርበው ክሣቸውን ያደምጣሉ፤ ተብሎ በሚጠበቅበት በዚኽ ወቅት፣ ክሡን በተመለከተ የሚደረገው ክርክር፣ እየተጠናከረ እና እየተሟሟቀ መጥቷል።

ትረምፕ፣ 37 ክሦች እንደሚቀርቡባቸው ይጠበቃል። የአገር መከላከያ መረጃዎችን የያዙ ዶሴዎችን በገዛ ፈቃዳቸው መያዝ፣ የሕግ ሒደትን ማደናቀፍ፣ ሤራ እና በሐሰት መመስከር የሚሉ ክሦች ይገኙበታል።

በኤቢሲ ቴሌቪዥን ቀርበው በተናገሩት፣ የሪፑብሊካኑ ሴናተር ሊንዚ ግራሃም አስተያየት፣ ክሡ፥ “የቀድሞውን ፕሬዚዳንት ሕጋዊ መብት ለማሳጣት የሚደረግ ሙከራ ነው።”

“ሰውዬውን ሰላይ ነው ብላችኹ ብትከሡትም፣ ለዶናልድ ትረምፕ ያለኝ ድጋፍ አይቀየርም። ፍርድ ቤት ጥፋተኛ እስከሚለው ድረስ፣ ንጹሕ ሰው ነው። ለአንተ ማስተላለፍ የፈለግኹት መልዕክት፣ አብዛኛው የሪፐብሊካን አባላት፣ ሕጉ፥ የፖለቲካ መሣሪያ ነው፤ ብለው ያምናሉ፤” ብለዋል ሊንዚ ግራሃም።

በልዩ መርማሪው ጃክ ስሚዝ፣ በምሥጢራዊ ሰነዶቹ ላይ የሚደረገው ምርመራ፣ ለፖለቲካ ጠቀሜታ ስለ መዋሉ፣ ምንም ማስረጃ የለም፤ ሲሉ፣ ሌላው በኤቢሲ ቴሌቪዥን የቀረቡት የዴሞክራሲ ፓርቲው ሴናተር ክሪስ ኩንስ ተናግረዋል።

“ፕሬዚዳንት ትረምፕ፣ ትላንት ምሽት፣ የፍትሕ መሥሪያ ቤቱን ነቅፈው፣ የፌዴራል ምርመራ ቢሮው በጀት እንዳይመደብለት ቢጠይቁም፣ በፍትሕ ሒደቱ የመዳኘት መብታቸው እንደሚከበርላቸው እተማመናለኹ። በስተመጨረሻም፣ እርሳቸውን ለመሰሉ የአሜሪካ ዜጎች የሚዋቀረው ፍርድ ሰጪ ቡድን፣ ክሣቸው በደንቡ መሠረት መካሔዱን፣ እንዲሁም የፌዴራሉን የወንጀል ሕግ መጣስ ወይም አለመጣሳቸውን ይወስናል፤” ሲሉ ተናግረዋል ኩንስ።

ትረምፕ፣ ንጹሕ ሰው እንደኾኑ፣ “ትሩዝ ሶሻል” በተሰኘው የማኅበራዊ ትስስር መድረካቸው አስታውቀዋል። ከትረምፕ ሌላ፣ የፌዴራል ክሥ የቀረበበት የቀድሞ ፕሬዚዳንት የለም።

በ”ፎክስ ኒውስ ሰንዴይ” ቃለ መጠይቅ የተደረገላቸውና በትረምፕ አስተዳደር ወቅት ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የነበሩት ዊሊያም ባር፣ የቀድሞውን ፕሬዚዳንት፣ “ደንታ ቢስ” ሲሉ በጽኑ ነቅፈዋል።

“በሌላ አገር ላይ ስለሚደረግ የውጊያ ጥቃት ዕቅድ ወይም የመከላከያ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የሰነደውን የመከላከያ ዐቅምን የተመለከቱ ሰነዶች፣ በምንም ዐይነት፣ የዶናልድ ትረምፕ የግል ዶሴዎች አይደሉም። እንደማስበው፣ መንግስት በሓላፊነት ተንቀሳቅሷል። ዶናልድ ትረምፕ፣ ዶሴዎቹን እንዲመልሱ፣ መንግሥት በቂ ዕድል ሰጥቷቸዋል፤” ብለዋል የቀድሞው ዐቃቤ ሕግ።

አሁን ባለው ኹኔታ፣ ከሪፐብሊካኖች ወገን፣ ለዶናልድ ትረምፕ ያለው ድጋፍ፣ በመጪው ምርጫ ፓርቲያቸውን በፕሬዝደንታዊ ዕጩነት ለመወከል የሚፎካከሩትን ጨምሮ፣ ጠንከር ያለ ነው።

በሲኤንኤን ቴሌቪዥን የቀረቡትና የሪፐብሊካን ፓርቲን፣ በፕሬዚዳንታዊ ዕጩነት ለመወከል የሚሹት ቪቬክ ራማስዋሚ፣ በክሡ ላይ እምነት እንደሌላቸው ይናገራሉ።

“በበኩሌ፣ ግልጽ ባልኾነው ክሥ ላይ እምነት የለኝም። በእርግጥ እውነት ከኾነ፣ የግለሰቡን መጥፎ ውሳኔ ያሳያሉ። እኔ ግን፣ ክሦቹ እውነተኛ ስለመኾናቸው ጥርጣሬ አለኝ። ዋናው ነገር ግን፣ የአንድን ግለሰብ መጥፎ ውሳኔ፣ ከሕግ መጣስ ጋራ ማገናኘት አንችልም፤” ይላሉ ራማስዋሚ።

ትረምፕ፣ በቀረበባቸው ክሥ ጥፋተኛ ኾነው ከተገኙ፣ እስር ይጠብቃቸዋል። የሕግ ባለሞያዎች እንደሚሉት ግን፣ ጥፋተኛ ኾነው ቢገኙ እንኳ፣ ለፕሬዚዳንትነት እንደገና ከመወዳደር የሚያግዳቸው ሕግ የለም።

XS
SM
MD
LG