ቱርክ ውስጥ ዛሬ ቅዳሜ በሮኬት እና ፈንጅዎች ማምረቻ ተቋም ላይ በደረሰ ፍንዳታ አንድ ህንጻ በመውደሙ በውስጡ የነበሩ አምስት ሠራተኞች መሞታቸውን አንድ የቱርክ ባለሥልጣን አስታወቁ፡፡
ፍንዳታው የደረሰው በአገሪቱ አቆጣጠር ዛሬ ጧት ለሶስት ሩብ ጉዳይ ላይ ከዋና ከተማዋ አንካራ ወጣ ብሎ በሚገኘው የመንግሥት ሜካኒካልና ኬሚካል ኢንደስትሪ ኮሮፖሬሽን ህንጻ ላይ ነው፡፡
አደጋው የተከሰተው ዳይናሚት በሚመረትበት ወቅት በውስጡ በተፈጠረ የኬሚካል እክል ምክንያት ሊሆን እንደሚችል የአንካራ አገረ ገዥ ቫሲብ ሳሂን ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡
አደጋው በደረሰበት ህንጻ አካባቢ የነበሩ ሱቆችና የመኖሪያ ቤቶች ከፍንዳታው ድምጽ የተነሳ መስኮቶቻቸው መሰባበሩን አሶሴይትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡