ሁለቱ የሱዳን ተፋላሚ ወገኖች ዛሬ ቅዳሜ በአገሪቱ የሰዓት አቆጣጠር ከማለዳው 12 ሰዓት ጀምሮ ተኩስ ለማቆም መስማማታቸው ተነገረ፡፡
ከዚህ ቀደም የነበሩት ስምምነቶች በሙሉ ተግባራዊ ባለመደረጋቸው የ24 ሰዓት የተኩስ አቁም ስምምነቱ ሊጣስ ይችላል የሚል ስጋት መኖሩ ተመልክቷል፡፡
የዛሬው ቅዳሜ የተኩስ አቁም ስምምነት ከተጣሰ ዩናይትድ ስቴትስ እና ሳዑዲ አረብያ የሚያደርጉትን የአደራዳሪነት ጥረት እንደሚያቋርጡ አስጠንቅቀዋል፡፡
“የአንድ ቀን የተኩስ አቁም ስምምነት ከምንጠብቀው እጅግ ዝቅተኛው ነው” ሲሉ የካርቱም ነዋሪ የሆኑት መሀመድ በሽር መናገራቸውን አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል፡፡
ነዋሪው “ይህ የተወገዘ ውጊያ እንዲቆም እንጠብቃለን” ማለታቸውንም ዘገባው አመልክቷል፡፡
ለሰዓታት የሚቆየው ስምምነት ለሰብአዊ እርዳታ ተደራሽነት መንገድ እንደሚከፍት ተነግሯል፡፡
በሁለቱ ጀኔራሎች አብዱል ፋታህ አልቡርሃን እና የቀድሞ ምክትላቸው በነበሩት ጀኔራል መሃመድ ሀምዳን ደጋሎ ኃይሎች መካከል የሚካሄደው ጦርነት የተጀመረው ባለፈው ሚያዝያ አጋማሽ ላይ ነው፡፡
በሱዳን ዋና ከተማ ካርቱምና አካባቢው በመካሄድ ባለው በዚህ ጦርነት ወደ 2ሺ የሚጠጉ ሰዎች ሲሞቱ 2 ሚሊዮን የሚጠጉት ደግሞ መፈናቀላቸው ተመልክቷል፡፡