በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በግብአት እጥረት ያለማዳበሪያ የዘሩ አርሶ አደሮች የምርት እጥረት እንዳይገጥማቸው ስጋታቸውን ገለጹ


የግብርና ሚኒስቴር
የግብርና ሚኒስቴር

በዘንድሮው ዓመት የመኸር እርሻ፣ የግብአት እጥረት እንዳጋጠማቸውና ያለማዳበሪያ እየዘሩ እንደኾነ አርሶ አደሮች ሲናገሩ፤ ግብርና ሚኒስቴር በበኩሉ፣ ችግሩን ለመፍታት፣ የማዳበሪያ ግዥ እንደፈጸመና በተለይም፣ በሰኔ እና በሐምሌ ለሚዘሩ አርሶ አደሮች፣ በቂ ማዳበሪያ ስለሚቀርብ ስጋት ሊገባቸው አይገባም፤ ብሏል፡፡

ከዐማራ ክልል ምዕራብ ጎጃም ዞን ሜጫ ወረዳ፣ ለአሜሪካ ድምፅ በስልክ አስተያየት የሰጡ አርሶ አደር፣ የግብአት እጥረት በማጋጠሙ፣ ማሳቸውን ያለማዳበሪያ ለመዝራት መገደዳቸውን ይናገራሉ፡፡ እጥረቱ ካልተቀረፈም፣ ወደፊት የምርት እጥረት እንዳይገጥማቸው ስጋቸውን አመልክተዋል፡፡

የወረዳው የግብርና ባለሞያ የኾኑት አቶ አለማ ዳኜ በበኩላቸው፣ ለወረዳው፣ 71 ሺሕ ኩንታል ማዳበሪያ ይቀርባል ተብሎ እንደነበር አውስተው፣ እንደተባለው ግን አለመቅረቡን ተናግረዋል፡፡ በዚኽ ምክንያት፣ አርሶ አደሮች፣ ያለማዳበሪያ መዝራታቸውን አስረድተዋል፡፡

ይህንኑ ችግራቸውን፣ በሰላማዊ ሰልፍ ለክልሉ መንግሥት ቢያቀርቡም፣ እስከ አሁን ድረስ ምላሽ አለማግኘቱን፣ የግብርና ባለሞያው አቶ አለማ ዳኜ አመልክተዋል፡፡ በዚኹ ከቀጠለ፣ በቀጣዩ ዓመት የምርት እጥረት ማጋጠሙ አይቀርም፤ ብለዋል፡፡

በግብአት እጥረት ያለማዳበሪያ የዘሩ አርሶ አደሮች የምርት እጥረት እንዳይገጥማቸው ስጋታቸውን ገለጹ
please wait

No media source currently available

0:00 0:08:29 0:00

የግብርና ሚኒስቴር በበኩሉ፣ የዐማራ ክልልን ጨምሮ በልዩ ልዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚነሣውን የግብአት እጥረት ለመቅረፍ እየሠራ እንደኾነ አስታውቋል፡፡ በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ፣ የኢንቨስትመንት እና የግብአት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ዶር. ሶፊያ ካሳ፣ ለአሜሪካ ድምፅ በሰጡት ቃለ መጠይቅ፣ መንግሥት፣ በ56ነጥብ7 ቢሊዮን ብር የማዳበሪያ ግዢ መፈጸሙን ጠቅሰዋል፡፡ እስከ አሁን ድረስም፣ ከተገዛው 12ነጥብ 8 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ ውስጥ፣ 5ነጥብ7 ሚሊዮኑ ኩንታሉ፣ ለአርሶ አደሮች መሠራጨቱንና ቀሪው ደግሞ በመጓጓዝ ላይ እንደኾነ፣ ዶር. ሶፊያ ገልጸዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት፣ አርሶ አደሮች፣ ማዳበሪያ ላይመጣ ይችላል የሚል ስጋት እንዳለባቸው እየሰሙ እንደኾነ የተናገሩት ዶር. ሶፊያ፣ በተለይም በሰኔ እና በሐምሌ ለሚዘሩ አርሶ አደሮች፣ በቂ ማዳበሪያ ስለሚቀርብ ስጋት ሊገባቸው አይገባም፤ ብለዋል፡፡

የምርጥ ዘር እጥረትም፣ በሀገር ደረጃ መኖሩን ያመለከቱት ዶር. ሶፊያ፣ አርሶ አደሮቹ ከሚፈልጉት የዘር መጠን ግማሹን እንኳ ማሟላት እንዳልተቻለ ተናግረው፣ ኾኖም፣ መንግሥት ጥረት እያደረገ እንዳለ ነው የገለጹት፡፡

አሁን ባለው፣ የግብአት እጥረት ምክንያት፣ በመጪው ዓመት የምርት እጥረት ያጋጥም እንደኾነ የተጠየቁት ዶ/ር ሶፊያ፣ ጉዳዩ የዳሰሳ ጥናት ይፈልጋል፤ ብለዋል፡፡

ከ2013 ዓ.ም. ጀምሮ፣ ጦርነት ላይ የነበረው የትግራይ ክልል፣ ከፕሪቶርያው ስምምነት በኋላ፣ የግብርና ግብአት ቀርቦለት እንደኾነም ተጠይቀዋል፡፡ ሚኒስትር ዴኤታዋ በሰጡት ምላሽ፣ ክልሉ፥ 800 ሺሕ ኩንታል ማዳበሪያ እንዲቀርብለት መጠየቁን ተናግረዋል፡፡ ከዚኽም ውስጥ እስከ አሁን፣ 100ሺሕ ኩንታል እንደተሰጠውና በሒደት ደግሞ ተገዝቶ እንደሚቀርብለት አመልክተዋል፡፡

/የዚህ ዘገባ ሙሉ ይዘት በተያያዘው የድምፅና ምስል ፋይል ውስጥ ይገኛል/

XS
SM
MD
LG