በአሮሚያ ክልል፣ ከሸገር ከተማ አስተዳደር ግንባታ ጋራ በተያያዘ፣ የመኖሪያ ቤቶች እና የእምነት ተቋማት የፈረሳ ሒደት፣ አስቀድሞ ውይይት ሳይደረግበት እንደተከናወነና ፍትሐዊ እንዳልኾነ፣ የአሜሪካ ድምፅ ያናገራቸው፣ የአካባቢው ነዋሪዎች እና የእምነት ተቋማት መሪዎች ገልጸዋል።
በጉዳዩ ላይ ምላሽ የሰጡን፣ የሸገር ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ጉግሳ ደጀኔ በበኩላቸው፣ ቤት የማፍረሱ ርምጃ፥ የሕግ የበላይነትን ለማስከበር፣ በመመካከር እና በመተማመን የተወሰደ እንደኾነና ይህም፣ በሕገ ወጥ መንገድ በተገነቡ ቤቶች ላይ እንጂ፣ ማንነትንና ሃይማኖትን ማዕከል ያደረገ አለመኾኑን በመጥቀስ አስተባብለዋል፡፡
በሌላ በኩል፣ በሸገር ከተማ እየተካሔደ ባለው የመሳጂዶች ፈረሳ ጉዳይ፣ ከኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ፕሬዚዳንት አቶ ሺመልስ አብዲሳ ጋራ፣ ሰፊ ውይይት ማድረጉን፣ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ም/ቤት አስታውቋል፡፡ የጠቅላይ ም/ቤቱ ፕሬዚዳንት ሼኽ ሐጂ ኢብራሂም ቱፋ፣ “አሁን ግን ችግሩ መፍትሔ ማግኘቱን” ተናግረዋል፡፡
በኦሮሚያ ክልል፣ በቅርቡ በተመሠረተው የሸገር ከተማ አስተዳደር፣ “ሕገ ወጥ ግንባታ” በሚል፣ ቤታቸው የፈረሰባቸው፣ አንድ ለደኅንነታቸው በመስጋት ስማቸዉ እንዳይገለጽ የጠየቁ የሱሉልታ ነዋሪ፣ ለአሜሪካ ድምፅ እንደተናገሩት፣ ከ20 ዓመት በላይ የቀን ሥራ ሠርተው የሠሩት ቤታቸው፣ “ሕገ ወጥ ግንባታ ነው፤” በሚል እንደፈረሰባቸው ተናግረዋል፡፡ የከተማ አስተዳደሩ ቤት የማፍረስ ርምጃም፣ “በማንነት ላይ ያነጣጠረ ነው፤” ሲሉም ቅሬታችውን ይገልጻሉ፡፡
ሌላው አስተያየት ሰጪያችን፣ አሁን “ትልቁ ገላን ክፍለ ከተማ” ተብሎ በተሰየመውና ልዩ ስሙ ሞጆ ዴራ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነዋሪ የነበሩና ቤታቸው የፈረሰባቸው ናቸው፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት፣ በአካባቢው፥ ከ10 ዓመት በላይ የኖሩ ቢኾንም፣ ቤታቸውን “ሕገ ወጥ ነው” ብለው እንዳፈረሱባቸው ተናግረዋል፡፡
አክለውም፤ “የሸገር ከተማ አስተዳደር እንደ ዐዲስ ሲቋቋም ውይይት የለም፤ ለሕዝቡም ምንም የተነገረ ነገር አልነበረም፡፡ ምንም የተሰጠን ማስጠንቀቂያ ሳይኖር፣ ጫት ቃሚ ወይም አልኮል ጠጪ የሚመስሉ፣ ከየጎዳናው የተሰበሰቡ፣ ብዛታቸው እሰከ 300 የሚደርሱ ወጣቶች በብዛት ይመጡና በቀጥታ ማፍረስ ይጀምራሉ፡፡ ምንም ማድረግ ስለማንችል፣ ወደ ውጭ ወጥተን እንቆማለን፡፡ ዛሬ ማፍረስ የጀመሩትን ሠፈር፣ ነገ ተመልሰውበት አይመጡም፡፡ ዕቃችንን ለማውጣት ስንል፣ የቀበሌ አስተዳዳሪዎችን፥ “ተመልሰው ይመጡ ይኾን?” ብለን ሰንጠይቃቸው፣ አናውቅም፤ ይሉናል፡፡” ብለውናል።
የአካባቢው ማኅበረሰብ ተወላጅ እንደኾኑ የሚገልጹት እኒህ አስተያየት ሰጪ፣ “የደረሰብን ጉዳት ኢኮኖሚያዊ ብቻ ሳይኾን፣ ማኅበራዊ እና ሥነ ልቡናዊ ጭምር ነው፤” ይላሉ፡፡
አያይዘውም፣ “በጣም የሚያሳዝነው፣ እኛ እንደ ሕዝብ፥ ሥነ ልቡናዊ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳት ነው የደረሰብን፡፡ በተለይ እንደ ኦሮሞ ሕዝብ በፖለቲካው፣ ሌሎች፥ የኦሮሞ አልፈረሰም፤ ይሉናል፡፡ ሥነ ልቡናዊው ጉዳት ደግሞ፣ ቤትኽ ፈረሰብኽ፤ ማለት፣ ራቁትኽን ቀረኽ፤ ማለት ነው፡፡”ብለዋል።
የሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም፣ በሸገር ከተማ አስተዳደር፣ “ሕገ ወጥ ግንባታ” በሚል እየተካሔደ ካለው የቤቶች ፈረሳ ጋራ የተያያዙ፣ 100ሺሕ አቤቱታዎች እንደቀረቡለት፣ የአሜሪካ ድምፅ መዘገቡ አይዘነጋም፡፡ የሰብአዊ መብቶች ተቋማት እና የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችም፣ ይህንኑ የፈረሳ ርምጃ ተቃውመው መግለጫ ማውጣታቸው የሚታወስ ነው፡፡
የመኖርያ ቤቶችን ብቻ ሳይኾን፣ የእምነት ተቋማትንም ባካተተው የፈረሳ ርምጃ፣ 22 መሳጂዶች፣ ያለምንም ማስጠንቀቂያ እንደፈረሱ፣ የኦሮምያ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት የመስጊዶች ጉዳይ ሓላፊ፣ ሼህ አብዱላኪም ሐጂ ሑሴን ገልጸዋል፡፡
በተመሳሳይ፣ የፕሮቴስታንት እምነት ተከታይ የኾኑ “የሰማያዊ ርስት ቤተ ክርስቲያን” መጋቢ ደረጄ ሺፈራው በበኩላቸው፣ የሸገር ከተማ አስተዳደር፣ ያለምንም ማሰጠንቀቂያ ቤተ ክርስቲያናቸውን እንዳፈረሱባቸው፣ ለአሜሪካ ድምፅ ተናግረዋል፡፡ መጋቢ ደረጀ እንደሚሉት፣ እሑድ የአምልኮ ሥርዐት ያከናወኑበት ቤተ ክርስቲያናቸው፣ በሌሉበት በቀጣዩ ዕለት ሰኞ ፈርሶባቸዋል፡፡
በተነሡት ቅሬታዎች እና አስተያየቶች ላይ፣ ለአሜሪካ ድምፅ ምላሽ የሰጡት፣ የሸገር ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ጉግሣ ደጀኔ፣ የቤት ፈረሳ ርምጃው የተወሰደው፣ የሕግ የበላይነትን ለማስከበር ነው፤ ይላሉ፡፡
“አብዛኞቹ ግንባታዎች፣ መንገድ ዘግተው የተሠሩ ናቸው ወይም በተራራዎች ላይ እና በደን ቦታዎች ላይ ነው የተገነቡት፡፡ ይህ ደግሞ፣ ለአገሪቱ ቀጣይነትም ኾነ ለትውልድ የሚጎዳ ስለኾነ፣ ኹኔታውን ማስተካከል፣ አስፈላጊ እና ግድ በመኾኑ፣ ተመካክረንና ተማምነን የተሠራ ሥራ ነው፡፡”
የተወሰደው ርምጃ፣ በግንባታዎቹ ሕገ ወጥነት ላይ ተመሥርቶ የተወሰደ እንጂ፣ ማንነትንም ኾነ ሃይማኖትን ማዕከል ያደረገ እንዳልኾነ፣ ምክትል ከንቲባው ተናግረዋል፡፡
“በከተማችን ውስጥ፣ በሕጋዊ መንገድ መሬት ወስደው፣ ቤት ሠርተው የሚኖሩ ብሔር ብሔረሰቦች አሉ፡፡ ሕጋዊ ኾነው እያለ ቤታችው የተነካባቸው ካሉ ማየት እንችላለን፤ ነገር ግን የሉም፡፡ ስለዚኽ፣ ማንም ኾነ ማን፣ መሬት የያዘበት ኹኔታ፣ ሕጋዊ ነው ወይም አይደለም የሚለውን ነው የምናየው፡፡ በሕገ ወጥ ግንባታ ላይ፣ የተለያዩ ማንነት ያላቸው ሰዎች ናቸው የተሳተፉት - ኦሮሞን ጨምሮ፡፡ ነገር ግን ማንም ይኹን ማን፣ ሕገ ወጥ ኾኖ እስከተገኘ ድረስ ርምጃ ተወስዶበታል፡፡”
ምክትል ከንቲባው፣ የማፍረስ ሒደቱ፣ “ያለምንም ማስጠንቀቂያ የተወሰደ ነው፤” በሚል የሚቀርበውን ቅሬታም አስተባብለዋል፡፡ “ከፈረሳው አስቀድሞ ውይይት ተደርጎበታል፤” ሲሉ፣ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
“ማስተር ፕላኑ ሲዘጋጅ፣ ማስረጃ ከማሰባሰብ ጀምሮ እስከ ዝግጅቱ ድረስ፣ በተለያየ መንገድ ሕዝብ ተወያይቶበታል፡፡ ይኸውም፣ በየአካባቢው ባሉ የሕዝብ ተወካዮች ተወያይተውበት ያጸደቁት ነው፡፡”
ባለፉት ሁለት ሳምንታት፣ በሸገር ከተማ፥ የመሳጂዶችን መፍረስ በማውገዝ፣ የጁመዓ ሶላት ሥነ ሥርዐት ከተጠናቀቀ በኋላ፣ ተቃውሞዎች ሲደረጉ ሰንብተዋል፡፡ በተለይም፣ በታላቁ አንዋር መስጊድ እና አካባቢው ፣ የሰዎች ሕይወት ማለፉንና በርካቶች መጎዳታቸውን፣ በጊዜው፣ ለአሜሪካ ድምፅ አስተያየት የሰጡ የዐይን እማኞች ተናግረዋል፡፡ በሌሎች አካባቢዎች በሚገኙ መሳጂዶችም እንዲሁ፣ የተቃውሞ እንቅስቃሴዎች ሲደረጉ ነበር፡፡
ይህንም ተከትሎ፣ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ም/ቤት፣ በሸገር ከተማ እየተካሔደ ባለው የመስጂድ ፈረሳ ጉዳይ፣ ከኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ፕሬዚዳንት አቶ ሺመልስ አብዲሳ ጋራ፣ ሰፊ ውይይት ማድረጉን፣ ትላንት በሰጠው መግለጫ አስታውቋል፡፡ በከተማ አስተዳደሩ፣ እስከ አሁን ድረስ 22 መሳጂዶች እንደፈረሱ፣ በመግለጫው ተመልክቷል፡፡
የጠቅላይ ም/ቤቱ ፕሬዚዳንት ሼኽ ሐጂ ኢብራሂም ቱፋ፣ አሁን ችግሩ፣ መፍትሔ ማግኘቱን ተናግረዋል፡፡ በውይይቱም፣ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት፥ ከእንግዲህ መፍረስ ያለባቸውን አብያተ እምነት፣ ራሳቸው የእምነት ተቋማቱ እንዲያፈርሱ እንጂ፣ በራሱ ማፍረስ እንደሚያቆም መስማማቱ ተገልጿል፡፡
የክልሉ ፕሬዘዳንት አቶ ሺመልስ፣ የሸገር ከተማ አስተዳደር፣ ሃይማኖታዊ ዕሤትን መሠረት አድርጎ እንደሚገነባና ለከተማዋ ፕላን የሚመጥኑ፣ በርካታ ዘመናዊ መሳጂዶች እንዲሠሩ ፍላጎታቸው እንደኾነ ተናግረዋል፡፡
በሸገር ከተማ አስተዳደር፣ በርካታ የመኖሪያ ቤቶች እና አብያተ እምነት፣ የሕግ የበላይነትን ለማስከበር የማፍረስ ርምጃ መውሰዱን ከማስታወቅ በቀር፣ ነዋሪዎችን መልሶ በማቋቋም ረገድም ኾነ ዘላቂ መፍትሔ በመስጠት በኩል፣ በሰብአዊ መብቶች ተቋማት ለሚቀርብበት ቅሬታ፣ እስከ አሁን ምንም ያለው ነገር የለም፡፡
/የዚህ ዘገባ ሙሉ ይዘት በተያያዘው የድምፅና ምስል ፋይል ውስጥ ይገኛል/