በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ሕጋዊ እና ሰላማዊ መንገዶች መገደባቸው ለሌሎች አማራጮች የሚያስገደድ እንዳይሆን የጋራ ምክር ቤቱ አሳሰበ


ሕጋዊ እና ሰላማዊ መንገዶች መገደባቸው ለሌሎች አማራጮች የሚያስገደድ እንዳይሆን የጋራ ምክር ቤቱ አሳሰበ
please wait

No media source currently available

0:00 0:06:47 0:00

ሕጋዊ እና ሰላማዊ መንገዶች መገደባቸው ለሌሎች አማራጮች የሚያስገደድ እንዳይሆን የጋራ ምክር ቤቱ አሳሰበ

በሕጋዊ እና ሰላማዊ አማራጮች ላይ ያለው ገደብ፣ ዜጎች እና የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ሌሎች አማራጮችን እንዲጠቀሙ እያስገደደ በመኾኑ ችግሩ እንዲቀረፍ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ጠየቀ፡፡

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት፣ ባለፈው ግንቦት 24 ቀን 2014 ዓ.ም. ባካሔደው አስቸኳይ ስብሰባ፣ በሕጋዊ እና ሰላማዊ አማራጮች ላይ ያለው ገደብ፣ ዜጎች እና የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ መብቶቻቸውን ለማስከበር ሌሎች አማራጮችን እንዲጠቀሙ የሚያስገድድ እየኾነ እንዳለ አጽንዖት የሰጠው የጋራ ምክር ቤቱ፣ በፖለቲካ ፓርቲዎች ላይ እየተደረገ ነው ያለው ጫና እንዲቆም ጠይቋል፡፡

ምንም እንኳን መንግሥት፣ የፖለቲካ ምኅዳሩ ስለ መስፋቱ ቢገልጽም፣ የጋራ ምክር ቤቱ፣ ነገሩ የተገላቢጦሽ እንደኾነ እንደሚያምን፣ ምክትል ሰብሳቢው ዶር. አብዱልቃድር አደም ተናግረዋል፡፡

የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤቱ፣ በዚኹ አስቸኳይ ስብሰባው፣ በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ያሉ ግጭቶች እና የፖለቲካ አለመረጋጋቶች፣ በኦሮሚያ ክልል ሸገር ከተማ አስተዳደር እየተፈጸመ ያለውን የቤቶች፣ የአብያተ እምነቶች እና ሌሎች ግንባታዎች ፈረሳ፣ የኑሮ ውድነት፣ የሙስና መንሰራፋት እና ሌሎችንም ልዩ ልዩ ወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች በተመለከተ ውይይት ማድረጉን አስታውቋል፡፡

ገዢውን የብልጽግና ፓርቲን ጨምሮ፣ 61 ሀገር አቀፍ እና ክልላዊ ፓርቲዎችን በሥሩ ማቀፉን የገለጸው ምክር ቤቱ፣ ዛሬ ዐርብ፣ ሰኔ 2 ቀን 2015 ዓ.ም. በሰጠው መግለጫ፣ ኢትዮጵያ በዘርፈ ብዙ የጸጥታ፣ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ እና ማኅበራዊ ችግሮች ውስጥ እንደምትገኝ ገልጾ፣ ባለ12 ነጥብ የአቋም መግለጫ አውጥቷል፡፡

ግጭቶችን በሰላም ከመፍታት አንጻር፣ በትግራይ ክልል አንጻራዊ ለውጥ እንደታየ የጠቀሰው መግለጫ፣ “በአማራ፣ በኦሮሚያ እና በጋምቤላ ክልሎች ያለው የሰላም ኹኔታ ግን፣ እጅግ አሳሳቢ ነው፤” ብሏል፡፡ በመኾኑም፣ በአገሪቱ ያሉ ግጭቶች ሁሉ፣ በድርድር እና በውይይት እንዲፈቱ ጠይቋል፡፡

የጋራ ምክር ቤቱ ባለ12 ነጥብ የአቋም መግለጫ ከዳሰሳቸው ጉዳዮች መካከል፣ ዜጎችን በኃይል የመሰወር ድርጊት አሳሳቢነት ይገኝበታል፡፡ እጅግ አሳሳቢ ኾኗል ያለው፣ የአፈና እና አስገድዶ የመሰወር ድርጊት እንዲቆም፣ የጋራ ምክር ቤቱ አሳስቧል፡፡

ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የመጣው፣ የመሠረታዊ ሸቀጦች የዋጋ ንረትም፣ ዜጎችን ለከፋ ጉዳት መዳረጉን ያብራራው የአቋም መግለጫው፣ ለዚኽም ዋና ምክንያት አድርጎ ያስቀመጣቸው፣ የፖሊሲ ችግር እና ሙስና፣ አስቸኳይ እልባት እንዲሰጣቸው ጠይቋል፡፡

የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሺዴ፣ የ2016 ዓመት በጀት ረቂቅን፣ ትላንት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረቡበት ወቅት፣ በጀቱ የዋጋ ንረትን መቀነስ በሚያስችል መንገድ መዘጋጀቱን፣ እንዲሁም መንግሥት ችግሩን ለመቆጣጠር፣ በገበያ ላይ ያለውን ገንዘብ መሰብሰብን ጨምሮ መሰል ርምጃዎችን እንደሚወስድ አብራርተዋል፡፡

በሸገር ከተማ ያለው የቤቶች እና የእምነት ተቋማት ፈረሳ ድርጊት ቆሞ፣ ሕጋዊ መንገድን እንዲከተል የጋራ ምክር ቤቱ በአቋም መግለጫው አሳስቧል፡፡

ለሀገሪቱ ውስብስብ ችግሮች፣ መፍትሔ ያመጣል ያለው፣ ሁሉን አቀፍ ብሔራዊ ውይይት፣ ግልጽ እና አሳታፊ በኾነ መንገድ እንዲካሔድም ጠይቋል፡፡

/የዚህ ዘገባ ሙሉ ይዘት በተያያዘው የድምፅና ምስል ፋይል ውስጥ ይገኛል/

XS
SM
MD
LG