በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

አል-ሻብብ በዶሎ የኢትዮጵያ ወታደራዊ ሠፈር ሊፈጽም የሞከረው የሽብር ጥቃት ከሸፈ


በኢትዮጵያ ሶማልያ ድንበር፣ ዶሎ አካባቢ በሚገኘው፣ የኢትዮጵያ ወታደራዊ ሠረፍ ላይ፣ አል-ሻባብ የሰነዘረውን ጥቃት ማክሸፏን፣ ኢትዮጵያ አስታወቀች።

ይኸው የአል-ሻብብ የጥቃት ሙከራ፣ የአጠፍቶ ጠፊ ቦምብ በተጠመደባቸው ሁለት ተሸከርካሪዎች አማካይነት ለመፈጸም የታቀደ እንደኾነ ሲገለጽ፤ የመጀመሪያው ፍንዳታ፥ በወታደራዊ ሰፈሩ መግቢያ በር ላይ መከሠቱን፣ ሁለተኛው ፍንዳታ ደግሞ፣ ከመጀመሪያው ጥቂት ራቅ ያለ ቦታ መታየቱን፣ አንድ ለደኅንነታቸው ሲሉ ማንነታቸውን መግለጽ ያልፈለጉ ነዋሪ፣ ለአሜሪካ ድምፅ ተናግረዋል።

እስላማዊው ጽንፈኛ ቡድን አል-ሻባብ፣ ዛሬ ረቡዕ፣ ግንቦት 30 ቀን 2015 ዓ.ም. በኢትዮ-ሶማሊያ ድንበር፣ ዶሎ አካባቢ፣ በኢትዮጵያ ወታደራዊ መደብ ላይ ሊፈጽም የነበረውን ጥቃት፣ ኢትዮጵያ ማክሸፏን፣ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።

ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ፣ ዛሬ ባወጣው መግለጫ፣ “ጥቃት አድራሾቹ፥ ጥቃት ከመፈጸማቸው በፊት፣ በመሥመራቸው ውስጥ ሳሉ፣ በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አስቀድሞ በተወሰደባቸው ርምጃ፣ ሙከራቸው ከሽፏል፤” ሲል አስታውቋል።

“የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት፣ የአሸባሪውን ቡድን አጥፍቶ ጠፊዎች እና መሣሪያቸውን፣ ሙሉ ለሙሉ አውድሟል፤” ብሏል ሚኒስቴሩ፡፡

ቀደም ብሎ፣ የሶማልያ ዶሎ ነዋሪዎች፣ ከከተማው ወጣ ብሎ በሚገኘው፣ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ካምፕ ላይ፣ ሁለት የፍንዳታ ጥቃቶች መድረሳቸውን አስታውቀዋል፡፡ ጥቃቶቹ፣ ከጠዋቱ አራት ሰዓት በፊት፣ በተከታታይ መፈጸማቸውን፣ የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል።

ለደኅንነታቸው ሲሉ ማንነታቸው እንዳይጠቀሰ የጠየቁ አንድ የአካባቢው ነዋሪ፣ የመጀመሪያው ፍንዳታ፥ በካምፑ መግቢያ አካባቢ፤ ሁለተኛው ደግሞ፥ ከመጀመሪያው ፍንዳታ ጥቂት ራቅ ብሎ መድረሱን ተናግረዋል፡፡ በሌላ የአካባቢው ነዋሪ የተቀረጸ ቪዲዮ፣ ከካምፑ አካባቢ ከፍተኛ ጢስ ሲወጣ ያሳያል፡፡ እኚሁ የዐይን እማኝ የቀረጹት የቪዲዮ ምስል ላይም፣ ሁለተኛው ፍንዳታ ይሰማል፡፡

የአልሻባብ ታጣቂ ቡድን፣ ሁለት የተሻሻሉ ፈንጂዎች የተገጠሙላቸውን ተሽከርካሪዎች፣ ከአጥፍቶ ጠፊዎች ጋራ አድርጎ መላኩን በመግለጽ፣ ለጥቃቱ ሓላፊነት ወስዷል፡፡ የሶማልያ የክላልዊ ደኅንነት ባለሥልጣን ኦስማን ኑህ ሃጂ፣ የኢትዮጵያ ወታደሮች፥ ሁለቱ ተሸከርካሪዎች ወደ ካምፑ ከመድረሳቸው በፊት ለማውደም መቻላቸውን፣ ለአሜሪካ ድምፅ ተናግረዋል።

“የፍተሻ ኬላው ከጦር ሠፈሩ ይርቃል፡፡ መኪናው እንዲቆም ቢጠየቅም፣ አልቆም ስላለ ወታደሮቹ የማስጠንቀቂያ ተኩስ ተኮሱበት፡፡ አሁንም አልቆመም፡፡” ያሉት ኦስማን ኑህ “ተሽከርካሪው ፈንጂ የጫነ መኾኑን እንዳወቁ ግን፣ ሚሳይል ተኩሰው አወደሙት፡፡ የተቃጠሉት፥ መኪናው እና አጥፍቶ ጠፊው ብቻ ናቸው፡፡” ብለዋል።

ባለሥልጣኑ አክለው እንደተናገሩት፣ መኪኖቹ፥ በከተማው አየር ጣቢያ የሚገኘውን የሶማሊያ እና የኢትዮጵያ ኃይሎች ካምፕ ለማፈንዳት ተቃርበው ነበር፤ ብለዋል፡፡

የአጥፍቶ ጠፊ ተሸከርካሪዎቹ ዓላማ፣ በአየር ጣቢያ ውስጥ ወደሚገኘው ወታደራዊ ካምፕ ዘልቆ በመግባት፣ በአውሮፕላኖች እና በወታደሮች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ለማድረስ እንደነበር ያመለከቱት ባለሥልጣኑ፣ እስከ አሁን ድረስ፣ በሲቪሎችም ሆነ በወታደሮች ላይ የደረሰ ጉዳት አለመኖሩን አስታውቀዋል፡፡ “እግዚአብሔር ይመስገን፡፡ በወታደሮችም ይኹን በሲቪሎች ላይ ጉዳት አልደረሰም፤” ብለዋል ባለሥልጣኑ፡፡

ይኹን እንጂ፣ በመንግሥት የሚተዳደረው የሶማልያ ብሔራዊ የዜና ተቋም-“ሶና”፥ የመጀመሪያው ፍንዳታ፣ በካምፑ በር ላይ መፈጸሙንና በአራት ወታደሮች ላይ አስከፊ ጉዳት መድረሱን ዘግቧል፡፡

XS
SM
MD
LG