በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የትግራይ ኃይሎች የጦር አካል ጉዳተኞች የተቃውሞ ሰልፍ አካሄዱ


የትግራይ ኃይሎች የጦር አካል ጉዳተኞች የተቃውሞ ሰልፍ
የትግራይ ኃይሎች የጦር አካል ጉዳተኞች የተቃውሞ ሰልፍ

የትግራይ ኃይሎች የጦር አካል ጉዳተኞች እንክብካቤ እየተደረገልን አይደለም በማለት በዛሬው እለት በመቐለ ከተማ ሰልፍ አካሄዱ። የጦር ጉዳተኞቹ በሁለት ወር ጊዜ ውስጥ ለሁለተኛ ግዜ ባካሄዱት በዚህ ሰልፍ "አመራሮች ረስተዉናል፣ ከእኛ ይልቅ በግል ህይወታቸው ተጠምደዋል፣ ቀጣይ የጉዳተኞች ህይወት ተረስቷል" ሲሉ ተደምጠዋል።

በዛሬው እለት በተካሄደው ሰልፍ ላይ የተሳተፉት በመቶዎች የሚቆጠሩ የጦር አካል ጉዳተኞች "በቂ የህክምና አገልግሎት እና በቂ ምግብ ማግኘት አልቻልንም" በማለት ተቃውሞ ያሰሙ ሲሆን ለጦር ጉዳተኞች ተብሎ የሚሰበሰበውን ሃብት አመራሮች እያባከኑት ነው በማለትም ቅሬታ አሰምተዋል።

ከመቐለ ከተማ ምስራቅ አቅጣጫ ላይ ከምትገኘው አይናለም የተሰኘች መንደር፣ ከ10 ኪሎሜትር በላይ በእግር ተጉዘው በመምጣት በከተማዋ ጎዳናዎች ላይ ጥያቄያቸውን ያሰሙት ሰልፈኞች፣ በክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ፅሕፈት ቤት ገብተው ጥያቄያቸውን ያቀረቡ ሲሆን፣ ከግዜያዊ አስተዳደሩ ፅሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አማኑኤል አሰፋ ጋር ተወያይተዋል።

ከውይይቱ በኃላ አቶ አማኑኤል በሰጡት መልስ፣ የጦር አካል ጉዳተኞቹን ጥያቄ ለመመለስ "ግዝያዊ አስተዳደሩ ከጦር ጉዳተኞች ጋር በመተባበር ይሰራል" ብለዋል። ለተጎጂዎቹ የህክምና አገልግሎት፣ በተለይ የአጥንት ሕክምና ለመስጠት፣ እቅድ ተይዞ እየተሰራ መሆኑንም የገለፁት ኃላፊው፣ በቀጣይ የጦር ጉዳተኞችን ህይወት ለማስተካከል በክልሉ የአርበኞች ኮምሽን ተቋቁማል በማለትም ምላሽ ሰጥተዋል።

የጦር አካል ጉዳተኞቹ ተመሳሳይ ሰልፍ ባለፈው መጋቢት ወር ላይም አካሂደው ነበር።

XS
SM
MD
LG