ሩሲያ፣ ሶማሊያ ከአልሸባብ አሸባሪ ቡድን ጋር የምታደርገውን ውጊያ ለመደገፍ፣ ለሶማሊያ ታጣቂ ኃይሎች ድጋፍ ለመስጠት ሀሳብ ማቅረቧን፣ የሶማሊያ ዲፕሎማቶች አርብ እለት አስታወቁ።
ለጋዜጠኞች መረጃ ለመስጠት ስልጣን እንደሌላቸው በመግለፅ ስማቸው እንዳይገለፅ የጠየቁት ዲፕሎማቶች እንደገለፁት፣ የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ ሀሳቡን ያቀረቡት ከሶማሊያ አቻቸው አብሺር ኦማር ጃማ ጋር በሞስኮ ተገናኝተው በተነጋገሩበት ወቅት ነው።
አንድ ዲፕሎማት ስለጉዳዩ ሲያስረጉ "ሩሲያ የሶማሊያ መንግስት ከአልሸባብ ጋር ለሚያደርገው ውጊያ፣ ለሶማሊያ ጦር ወታደራዊ ቁሳቁሶችን ለማቅረብ ዝግጁ ናት" ብለዋል። ሆኖም ዲፕሎማቱ፣ ሩሲያ ምን አይነት መሳሪያዎችን፣ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ለረጅም ጊዜ የቆየ የጦር መሳሪያ እግድ ለተጣለባት ሶማሊያ እንዳቀረበች አልገለፁም።
እ.አ.አ በ1992፣ በሶማሊያ የተከሰተውን የእርስ በእርስ ጦርነት ተከትሎ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በሀገሪቱ ላይ የጦር መሳሪያ ማዕቀብ የጣለባት ሲሆን እ.አ.አ በ2013 የሶማሊያ ሰራዊት ከእስላማዊ ታጣቂዎች ጋር የሚያደርጉትን ውጊያ ለማገዝ፣ እግዱ በከፊል ተነስቶላታል።