በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ባለሥልጣኑ በማኅበረ ቅዱሳን ቴሌቪዥን ጣቢያ ላይ ያሳለፈውን ጊዜያዊ እግድ ማንሣቱን አስታወቀ


የማኅበረ ቅዱሳን አርማ
የማኅበረ ቅዱሳን አርማ

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን፣ ካለፈው ግንቦት 13 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ በማኅበረ ቅዱሳን የቴሌቪዥን ጣቢያ ላይ አስተላልፎት የነበረውን ጊዜያዊ እግድ ማንሣቱን፣ ዛሬ አስታውቋል፡፡

የመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣኑ፣ ጊዜያዊ እግዱን ማንሣቱን ያስታወቀው፣ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት፣ በቴሌቪዥን ጣቢያው ላይ የተላለፈው ውሳኔ፣ ተገቢነት እንደሌለው ገልጾ ባለሥልጣኑ ጊዜያዊ እግዱን እንዲያነሣ፣ ዛሬ ዐርብ ጠዋት፣ ግንቦት 18 ቀን 2015 ዓ.ም. በጻፈው ደብዳቤ መጠየቁን ተከትሎ ነው፡፡

የማኅበረ ቅዱሳን ቴሌቪዥን፣ አንዱ የቤተ ክርስቲያኒቱ ልሳን እንደኾነ የጠቀሰው የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤቱ፣ የጣቢያው ሥርጭቶች ችግር አለባቸው ከተባለ በቤተ ክርስቲያኒቱ ሕግ እና ሥርዐት እንደሚታይ ጠቅሷል፡፡

ስለ ወቅታዊ የቤተ ክርስቲያን ችግር፣ ግንቦት 13 ቀን 2015 ዓ.ም. በ“ሰበር ዜና” ካስተላለፈው መግለጫ ጋራ ተያይዞ የተላለፈው ጊዜያዊ እግድም፣ በመገናኛ ብዙኃን ዐዋጅ ቁጥር 1238/2013 ላይ በተደነገገው አንቀጽ 76 ንዑስ ቁጥር 1 እና 2 መሠረት፣ ከእግዱ በፊት ምንም ዐይነት ማስጠንቀቂያ ሳይደርሰውና ማኅበሩም በጉዳዩ ላይ አስተያየት እንዲሰጥ ሳይደረግ የተላለፈ ጊዜያዊ እግድ ተገቢ ባለመኾኑ እንዲነሣ ጠይቋል፡፡

ባለሥልጣኑ፣ ዛሬ ከቀትር በኋላ በምክትል ዋና ዲሬክተሩ ግዛው ተስፋዬ ቶላ ተፈርሞ በአድራሻ ለማኅበረ ቅዱሳን ቴሌቪዥን ጣቢያ በጻፈው ደብዳቤው፣ ጊዜያዊ እግዱን ያነሣው፣ ይህንኑ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት ጥያቄ መሠረት በማድረግ እንደኾነ ገልጿል፡፡

የሃይማኖት ብዙኃን መገናኛዎች፣ ሃይማኖታዊ አስተምህሯቸውን ለኅብረተሰቡ ሲያቀርቡ፣ ሕግንና ሥርዐትን አክብረው በማስከበር አርኣያ መኾንና አሉታዊ ውጤት ካላቸው አሉታዊ ይዘቶች መጠበቅ እንዳለባቸው፣ ባለሥልጣኑ በደብዳቤው አመልክቷል፡፡

የማኅበረ ቅዱሳን ቴሌቪዥን ጣቢያም፣ ሥርጭቶቹን በከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲያከናውንና በበላይነት የሚቆጣጠረው የጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤትም፣ በቀጣይ አስፈላጊውን ክትትል እንደሚያደርግ እምነት እንዳለው በመግለጽ፣ በማኅበሩ ላይ የሰጠውን ጊዜያዊ እግድ ማንሣቱን አስታውቋል፡፡

ከ2012 ዓ.ም. ጀምሮ የ24 ሰዓት የቴሌቪዥን ሥርጭት በማከናወን ላይ የሚገኘው ማኅበረ ቅዱሳን፣ ጊዜያዊ እግዱን በመቃወም ለባለሥልጣኑ አቅርቦት በነበረው ቅሬታ፣ የቤተ ክርስቲያኒቱን አስተምህሮ፣ የአገሪቱን ሕጎች እና የብዙኃን መገናኛ ዐዋጅ በመጠበቅ፣ ወቅታዊ መረጃዎችን የማድረስ፣ ምእመናንን በሃይማኖት የማጽናት፣ ለሀገር ሰላም እና አንድነት አዎንታዊ አስተዋፅኦ የማድረግ አገልግሎቱን በከፍተኛ ሓላፊነት እየፈጸመ እንደሚገኝ ማስታወቁ ይታወሳል፡፡

XS
SM
MD
LG