ሱዳንን ወደ ትርምስ የከተተው እና ከአንድ ሚሊዮን የሚበልጡ ሰዎችን ያፈናቀለው ጦርነት ስድስተኛ ሳምንቱን ባስቆጠረበት በአሁኑ ሰዓት የሀገሪቱ ጦር እና የፈጥኖ ደራሹ ጦር ተፋላሚ ኃይሎች ለሰባት ቀናት የሚቆይ የተኩስ አቁም ስምምነት መፈራረማቸው ተሰምቷል ።
የተኩስ አቁሙ በካርቱም አቆጣጠር ሰኞ ከምሸቱ 3፡45 ጀምሮ ተግባራዊ መደረግ እንደሚጀምር ንግግሩን የደገፉት ዩናይትድ ስቴትስ እና ሳዑዲ አረቢያ በጋራ በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል ።
ከዚህ ቀደም የተገቡ በርካታ የተኩስ አቁም ስምምነቶች ተጥሰዋል። ይሁን እንጂ የአሁኑ ስምምነት በዩኤስ-ሳውዲ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚደገፍ የክትትል ስርዓት ተፈጻሚ እንደሚሆን ተሰምቷል። መግለጫው ዝርዝር ጉዳዮችን አላብራራም ።
ስምምነቱ ሰብዓዊ እርዳታን ማዳረስ ፣ አስፈላጊ አገልግሎቶችን ወደ ነበሩበት መመለስ እና ኃይሎችን ከሆስፒታሎች እና አስፈላጊ የህዝብ መገልገያዎች ማስወጣትን ይመለከታል ።
የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ፣ "ጠመንጃን ዝም ለማሰኘት እና ያልተደናቀፈ ሰብአዊ አገልግሎት ለመስጠት ጊዜው ረፍዷል። ሁለቱንም ወገኖች ይህንን ስምምነት እንዲያከብሩ እማፀናለሁ - የዓለም አይኖች እየተመለከቱ ነው" ስለ ማለታቸው ሮይተርስ ዘግቧል ።