በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በትግራይ ክልል ጦርነቱ በፈጠረው ክፍተት ኤች.አይ.ቪ ከፍተኛ ሥርጭት ማሳየቱ ተገለጸ


በትግራይ ክልል ጦርነቱ በፈጠረው ክፍተት ኤች.አይ.ቪ ከፍተኛ ሥርጭት ማሳየቱ ተገለጸ
please wait

No media source currently available

0:00 0:04:51 0:00

በትግራይ ክልል ጦርነቱ በፈጠረው ክፍተት ኤች.አይ.ቪ ከፍተኛ ሥርጭት ማሳየቱ ተገለጸ

  • ጾታዊ ጥቃት ከተፈጸመባቸው ሴቶች አምስት በመቶዎች ከቫይረሱ ጋራ እንደሚኖሩ በምርመራ ተረጋግጧል፤

በትግራይ ክልል፣ በጦርነቱ ምክንያት በተፈጠረው ክፍተት፣ የቫይረሱ መዛመት በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ ስለመኾኑ ምልክቶች መኖራቸውን፣ የክልሉ ጤና ቢሮ የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ መከላከያ እና መቆጣጠርያ አስተባባሪ ገለጸ፡፡

አስተባባሪው አቶ ፍሥሓ ብርሃነ፣ ለአሜሪካ ድምፅ በሰጡት ማብራርያ፥ ከጦርነቱ በፊት የፀረ-ኤች.አይ.ቪ መድኃኒት ተጠቃሚ ከነበሩ ከ46 ሺሕ በላይ ሰዎች መካከል 13 ሺሕ የሚኾኑቱ፣ የት እንዳሉ አናውቅም፤ ብለዋል፡፡

በመቐለ ከተማ የሚገኘው ተስፋ ሕይወት የሴቶች ኤች.አይ.ቪ ፖዘቲቭ ማኅበር በበኩሉ፣ በጦርነቱ ጊዜ በመድኃኒት ዕጦት፣ 19 አባላቱ እንደሞቱበት ገልጿል፡፡ ለማኅበሩ አባላት፣ የጦርነቱ ወራት ከባድ እንደነበሩና ከሰላም ስምምነቱ በኋላ ግን የተሻለ ተስፋ ማግኘቱን ማኅበሩ አመልክቷል፡፡

በትግራይ ክልል ጤና ቢሮ የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ መከላከያ እና መቆጣጠሪያ አስተባባሪ አቶ ፍሥሓ ብርሃነ፣ ለአሜሪካ ድምፅ በሰጡት ማብራርያ፥ በክልሉ፣ ከጦርነቱ በፊት የቫይረሱን ሥርጭት ለመቆጣጠር ከፍተኛ እንቅስቃሴ ይደረግ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

ኾኖም፣ የክልሉ የጤና ዘርፍ በጦርነቱ ምክንያት በከፍተኛ ኹኔታ በመውደሙ፣ በትግራይ የፀረ-ኤች.አይ.ቪ መድኃኒት ተጠቃሚዎች፣ ከሩብ በላይ የሚኾኑቱ ያሉበትን ኹኔታ ማወቅ እንዳልተቻለ አስተባባሪው ገልጸዋል::

ጦርነቱ በተካሔደባቸው ጊዜያት፣ የዓለም ጤና ድርጅት(WHO)፣ ወደ ክልሉ ካስገባው በመጠን ውሱን የፀረ-ኤች.አይ.ቪ መድኃኒት በቀር፣ ከፍተኛ እጥረት እንደነበረም፣ አቶ ፍሥሓ አውስተዋል፡፡ ከሰላም ስምምነቱ በኋላ ግን፣ ወደ ክልሉ የፀረ-ኤች.አይ.ቪ መድኃኒት መግባት መጀመሩን አስታውቀዋል፡፡

በመቐለ ከተማ እና አካባቢዋ የሚንቀሳቀሰውና ከአንድ ሺሕ በላይ አባላት ያሉት፣ ተስፋ ሕይወት የሴቶች ኤች.አይ.ቪ ፖዝቲቭ ማኅበር ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ መልክኣ ኣስገዶም፣ ለእርሳቸው እና ለማኅበሩ አባላት፣ የጦርነቱ ዓመታት ከባድ እንደነበሩ አስረድተዋል፡፡

የሰሜን ኢትዮጵያን ጦርነት ተከትሎ፣ በክልሉ ቫይረሱ በከፍተኛ ደረጃ እየተዛመተ እንደሚገኝ ጠቋሚ ምልክቶች መኖራቸውን የገለጹት አቶ ፍሥሓ፣ በጦርነቱ ወቅት በሴቶች ላይ የተፈጸመው ጾታዊ ጥቃት እና በኢኮኖሚያዊ ችግር ምክንያት ወደ ወሲብ ንግድ የሚገቡ ሴቶች ቁጥር መጨመሩን አብራርተዋል፡፡

በክልሉ፣ በተወሰነ መልኩ የቫይረሱ ምርመራ እየተካሔደ ነው፤ ያሉት አስተባባሪው፣ በዚኽም ሥርጭቱ የመጨመር አዝማሚያ እንደሚያሳይ አመልክተዋል፡፡ ጾታዊ ጥቃት ከተፈጸመባቸው ሴቶችአምስት በመቶዎቹቫይረሱ በደማቸው እንዳለ በምርመራ መረጋገጡን ገልጸዋል፡፡ የሥርጭት መጠኑን በትክክል ለማወቅም፣ በቀጣይ ሰፊ ጥናት እንደሚያፈልግ፣ አቶ ፍሥሓ ተናግረዋል፡፡

ተስፋ ሕይወት የሴቶች ኤች.አይ.ቪ ፖዝቲቭ ማኅበር ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ መልክኣ በሰጡት አስተያየት፣ ከሰላም ስምምነቱ በኋላ የተሻለ ተስፋ እንዳገኙ ገልጸዋል፡፡

በአሁኑ ጊዜ በክልሉ ጥቅም ላይ እየዋለ ያለው የቫይረሱ መመርመርያ፣ ለክልሉ ለባለሞያዎች ዐዲስ መኾኑን የጠቀሱት አቶ ፍሥሓ ብርሃነ፣ የመመርመሪያውን አጠቃቀም አስመልክቶ ሥልጠና እየተሰጣቸው እንደኾነ አስታውቀዋል፡፡

XS
SM
MD
LG