በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የ34 ዓመታት የቅርስ ባለአደራው የአቶ አብዱላሂ “ሸሪፍ የግል ሙዚየም”


የ30 ዓመታት የቅርስ ባለአደራው አቶ አብዱላሂ “ሸሪፍ የግል ሙዚየም”
please wait

No media source currently available

0:00 0:08:04 0:00

የ30 ዓመታት የቅርስ ባለአደራው አቶ አብዱላሂ “ሸሪፍ የግል ሙዚየም”

ዓመታዊው “የጀጎል የሕይወት ዘመን ሽልማት” የመጀመሪያ አሸናፊ

የሐረሪ ክልል የሸዋል ዒድ በዓል በሚከበርበት ወቅት፣ “ዓመታዊ የጀጎል ሽልማት” መጀመሩን አስታውቆ ነበር። ለመጀመሪያ ጊዜ በተዘጋጀው የዘንድሮው ሽልማት፣ ቀዳሚ ተሸላሚ ያደረገው የ70 ዓመት የዕድሜ ባለጸጋውን አቶ አብዱላሂ ዓሊ ሸሪፍን ነው።

አቶ አብዱላሂ፣ በአገሪቱ ብቸኛው እና ትልቁ የግል ሙዚየም ባለቤት ሲኾኑ፣ በሙዚየሙ ስብስብም በክልሉ ካሉ አራት የመንግሥት ሙዚየሞችም ኾነ በአገራችን፣ በዐዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሥር ካለው ኢትኖግራፊክ ሙዚየም በመቀጠል በሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ነው፡፡ “ሸሪፍ የግል ሙዚየም”፣ በየዓመቱ ከ10ሺሕ በማያንሱ የቅርስ አፍቃሪዎች ይጎበኛል፡፡

የአሜሪካ ድምፁ ዐዲስ ቸኮል፣ ዘንድሮ የተጀመረው የጀጎል ሽልማት መርሐ ግብር ከመጀመሩ በፊት፣ በአቶ አብዱላሂ “ሸሪፍ የግል ሙዚየም” ተገኝቶ አጭር ቆይታ አድርጎ ነበር።

የሐረሪ ክልል፣ በርእሰ መስተዳድሩ አቶ ኦርዲን በድሪ በኩል፣ ለመጀመሪያ ጊዜ ይፋ የኾነውን ዓመታዊውን “የጀጎል ሽልማት”፣ ለአቶ አብዱላሂ ዓሊ ሸሪፍ ሰጥቷል።

ከ13ሺሕ በላይ ልዩ ልዩ ባህላዊ፣ ታሪካዊ፣ ሃይማኖታዊ ቅርሶችን ያሰባሰቡትና የሚከባከቡት አቶ አብዱላሂ፣ ከዚኽ ቀደምም፣ ከተለያዩ ተቋማት እና ግለሰቦች፣ በርካታ ሽልማቶችን አግኝተዋል፡፡ “የዓመቱ የበጎ ሰው”፣ “የዓመቱ አርዓያ ሰው”፣ የቅርስ ጥበቃ ልዩ እውቅና እና ሽልማት፣ የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ሰብእ እና ኅብረተሰብ ሳይንስ የክብር ዶክትሬት እና ልዩ ልዩ የገንዘብ እና ቁሳቁስ ሽልማቶች ይጠቀሳሉ፡፡

አቶ አብዱላሂ፣ ለሽልማት ዐዲስ ባይኾኑም፣ “የጀጎል ሽልማት”ን ግን በልዩ ኹኔታ እንደሚያዩት፣ ሽልማቱን በተቀበሉበት ወቅት ተናግረዋል።በግል መኖሪያ ቤታቸው ሲያሰባስቡት የቆዩት ቅርስ፣ በሒደት የግል ሙዚየም ወደ መክፈት አድርሷቸዋል። በቅርስ ስብስቦቻቸው መልኮች ላይ፣ የሐረሪ ቅርሶች ቁጥር በዝቶ ቢታይም፣ የሁሉም ብሔር ብሔረሰቦችንና ሃይማኖቶችን ቅርሶች ለማሰባሰብ ጥረት አድርገዋል፡፡ ይኸውም፣ ሐረሪ ያልኾኑ ኢትዮጵያውያን፣ በእርሳቸው ላይ ትልቅ እምነት ስላሳደሩ መኾኑን አቶ አብዱላሂ ይናገራሉ።

ከኢማም አሕመድ ጀምሮ፣ የዐፄ ቴዎድሮስ፣ የዐፄ ምኒልክ እና የቀዳማዊ ዐፄ ኃይለ ሥላሴ ዕድሜ ጠገብ ጎራዴዎችን ጨምሮ ያለፉ የአገሪቱ መሪዎች መገልገያዎች፣ በእጅ የተጻፉ ቅዱስ ቁርዐን፣ ከአንድ ሺሕ ዓመት በላይ ዕድሜ ያላቸው በአረብኛ እና በልዩ ልዩ ቋንቋዎች የተጻፉ መጻሕፍት፣ ሕገ መንግሥት፣ የጥንት የሐረሪዎች መገበያያ ገንዘብ፣ በአንድ ላይ የተሰበሰቡ ከ600 ሰዓት በላይ የጥንት የሐረሪ ሙዚቃዎች ታሪካዊ የሴቶች አልባሳት የመሳሰሉት በሙዚየሙ ውስጥ ተካብተው ይገኛሉ፡፡

በአሁኑ ሰዓት ሙዚየሙ የሚገኘው፣ በሐረር ጀጎል ውስጥ በሚገኘውና በ1903 ዓ.ም. የተገነባው የቀድሞው የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መኖሪያ ቤት ውስጥ ነው። አምስት የዐውደ ትዕይንት ክፍሎች እና ሁለት መጋዘንን ጨምሮ ብዙ ክፍሎችን የያዘ ሙዚየም እንደኾነ አቶ አብዱላሂ ይገልጻሉ።

በየጊዜው በቁጥር እና በዐይነት እየጨመረ ለሚሔዱት ስብስቦቻቸው፣ አሁንም ተጨማሪ ቦታ እንደሚያስፈልጋቸው የሚያመለክቱት አቶ አብዱላሂ፣ ቅርሶችን ከመጠበቅ ባሻገር እድሳት እና ክብካቤም እንደሚያደርጉ ይናገራሉ። ባለፈው ዓመት፣ በተደረገላቸው የሦስት ሚሊዮን ብር ድጋፍ፣ የቤት እድሳት እና መጻሕፍት ጥገና አድርገዋል፡፡ በዚኽም፣ “ሸሪፍ የግል ሙዚየም” ከበርካታ ሙዚየሞች የተሻለ አያያዝ እንዳለው ያስረዳሉ።

የቅርስ ስብስቦቻቸውን ለመጠበቅ እና በዘመናዊ መልኩ ለመያዝ፣ የአሜሪካ ኤምባሲን ጨምሮ ልዩ ልዩ አካላት፣ ለአቶ አብዱላሂ ድጋፍ አድርገዋል፡፡ ከ1ሺሕ300 በላይ መጻሕፍትን ዲጅታላይዝ አድርገው በሐርድ ዲስክ አስቀምጠዋል፡፡

የ70 ዓመት የዕድሜ ባለጸጋው አቶ አብዱላሂ፣ የ“ጀጎል የሕይወት ዘመን ሽልማት”ን በተቀበሉበት ወቅት፣ ቅርሶችን ለዓመታት በመኖሪያቸው ሲያሰባስቡ ያገዟቸውን የአስም ሕመምተኛ የኾኑ ባለቤታቸውን ጨምሮ፣ በእርሳቸው ታምነው ቅርሶቻቸውን የሰጧቸውን ሁሉ በልዩ ኹኔታ አመስግነዋል።

የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ምእመናን፣ በሌሎች ቦታዎች በቀላሉ የማያገኟቸው ሃይማኖታዊ ቅርሶች፣ በእርሳቸው “ሸሪፍ የግል ሙዚየም” ለመገኘት የቻሉት፣ ቅርሶቹን በአደራ የሰጧቸው ግለሰቦች፣ “በእኔ ላይ ካላቸው እምነት የተነሳ ነው፤” ይላሉ።

ብዙ ሰዎች፣ ቢሸጡት በርካታ ገንዘብ የሚያወጣላቸውን ቅርስ፣ እርሳቸው ዘንድ በማስቀመጣቸው፣ “ሸሪፍ የግል ሙዚየም” በአሁኑ ወቅት ካለው የቅርስ ስብስብ 2/3ኛ የሚኾነው በስጦታ የተካበተ መኾኑን ያስረዳሉ፡፡ ይህን ታማኝነት ለማትረፍ ግን፣ ከ34 ዓመታት ያላነሰ ያልተቋረጠ ትጋትን ጠይቋቸው እንደነበር አቶ አብዱላሂ ዓሊ ሸሪፍ አስታውሰዋል።

XS
SM
MD
LG