በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ከኢኮኖሚው ጂኦፖለቲካው እንዳመዘነበት የተነገረው የኢሳይያስ አፈ ወርቂ የቻይና ጉብኝት


ከኢኮኖሚው ጂኦፖለቲካው እንዳመዘነበት የተነገረው የኢሳይያስ አፈ ወርቂ የቻይና ጉብኝት
please wait

No media source currently available

0:00 0:03:08 0:00

ከኢኮኖሚው ጂኦፖለቲካው እንዳመዘነበት የተነገረው የኢሳይያስ አፈ ወርቂ የቻይና ጉብኝት

የኤርትራ ፕሬዚዳንት ኢሳይያስ አፈ ወርቂ፣ በቻይና እያደረጉት ያሉት ጉብኝት፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ዓላማ እንዳለው፣ የኤርትራ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ተንታኝ ዳን ኮኔል፣ ለአሜሪካ ድምፅ ገለጹ። "ዋና ዓላማው ግን፣ ፖለቲካዊ ነው፤" ያሉት ኮኔል፣ ኢሳይያስ፥ የቻይና ጉብኝታቸውን፣ አሁንም ዓለም አቀፍ ድጋፍ እንዳላቸው ለማሳየት ሊጠቀሙበት ይችላሉ፤ ሲሉ አስተያየት ሰጥተዋል።

ካለፈው እሑድ፣ ግንቦት 2 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ፣ በቻይና ጉብኝት እያደረጉ የሚገኙት ኢሳይያስ አፈ ወርቂ፣ “በአጠቃላይ በዓለም ያለውን ሥርዐት ወደተሻለና ፍትሐዊ ግንኙነት ለመቀየር፣ የቻይና ሕዝባዊ ሪፐብሊክ አስተዋፅኦ፣ ሌሎችን የሚያደፋፍር ነው፤” ሲሉ መናገራቸው ይታወሳል።

ከቻይናው ፕሬዚዳንት ሺ ጂንፒንግ የቀረበላቸውን ግብዣ ተቀብለው፣ ባሳለፍነው እሑድ ወደ ቻይና የተጓዙት ፕሬዚዳንት ኢሳይያስ አፈ ወርቂ፣ ቤጂንግ ሲደርሱ፣ በታላቁ የሕዝብ አዳራሽ ከፍተኛ አቀባበል ተደርጎላቸዋል። ኢሳይያስ ወደ ቻይና የተጓዙት፣ ከኤርትራ የውጭ ጉዳይ፣ የገንዘብ እና ልማት፣ እንዲሁም የንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስትሮች ጋራ ሲኾን፤ ሁለቱም ሀገራት አሸናፊ የሚኾኑበትን ትብብር ማጠናከር እና ስትራቴጂያዊ አጋርነታቸውን ማጎልበት እንደሚኖርባቸው፣ የቻይናው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሊ ቻንግ ተናግረዋል።

ይህን ጉብኝታቸውን አስመልክቶ፣ የአሜሪካ ድምፅ ያነጋገራቸው፣ የኤርትራ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ተንታኝ እና በኤርትራ ጉዳይ ስድስት መጻሕፍትን ያሳተሙት ዳን ኮኔል፣ የጉብኝቱ ዓላማ፥ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ይዘት ያለው ቢኾንም፣ ፖለቲካዊ ዓላማው እንደሚያመዝን አመልክተዋል።

"ኤርትራ በኢኮኖሚ ጉዳዮች እየተጎዳች ነው። ኢሳይያስ ከንግድ ሚኒስትሩ ጋራ ለመገናኘት ቀጠሮ የተያዘላቸው ለዚያ ይመስለኛል። ዋናው ዓላማ ግን ፖለቲካዊ ነው። ቻይና፣ በአፍሪካ ድጋፍ ለማግኘት እየሞከረች ነው።” ያሉት ዳን ኮኔል፣ “የኤርትራ ድምፅ ደግሞ ለሽያጭ የቀረበ በመኾኑ፣ ኢሳይያስ የኾነ ስምምነት ላይ ለመድረስ ነው ወደዚያ ያቀኑት። [በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት]ጠቅላላ ጉባኤ፣ ለቻይና ድጋፍ በመስጠት፣ ቻይና ኤርትራን እንድትደግፍ ማድረግ፤ ቻይና ደግሞ ድጋፏን እንደምትሰጥ ከአሁኑ አመላክታለች።" ብለዋል።

ቻይና፣ በአፍሪካ ቀንድ ያላትን ተጽእኖ ለማሳደግ በምትጥርበት ወቅት፣ በቀይ ባሕር ላይ የምትገኘው ኤርትራ ያላት መልክአ ምድራዊ አቀማመጥ ሳቢ ነው፡፡ ኤርትራ፣ በሰሜን ለስዊዝ ካናል እና ለአውሮፓ፣ እንዲሁም በደቡብ ምሥራቅ ከአረብ ባሕረ ሠላጤ እና ከሕንድ ውቅያኖስ ያላት ቅርበት ለቻይና አማላይ ነው። ከስድስት ዓመታት በፊት ወታደራዊ መደብ ያቋቋመችባት ጅቡቲ፣ ከኤርትራ ጋራ መዋሰኗም ለቻይና ሌላው ሳቢ ጉዳይ ነው።

ኮኔል እንደሚሉት ግን፣ ኢሳይያስ አሁን በቻይና የሚያደርጉት ጉብኝት፣ ለኤርትራ፥ "የተለየ የመዋዕለ ነዋይ ወይም የኢኮኖሚ ጥቅም" ይኖረዋል ብለው የማያስቡት ዳን ኮኔል፣ “በርግጥ በእጃቸው የኾነ ነገር ይዘው ስለኾነ የተጓዙት፣ አንድ ትንሽ ነገር ሊኖር ይችላል። ያን ያህል ለውጥ የሚያመጣ ግን አይኾንም። ምክንያቱም፣ ኤርትራ መዋዕለ ነዋይ ለማፍሰስ፣ ሳቢ የኾነ መሠረተ ልማትም ኾነ ሀብት የላትም - ከማዕድን ውጪ። ያን ደግሞ ቻይና ተቆጣጥራዋለች።" ይላሉ።

ኢሳይያስ የቻይና ጉብኝታቸውን፣ አሁንም፣ ዓለም አቀፍ ድጋፍ እንዳላቸው ለማሳየት እና ለዩናይትድ ስቴትስ አላቸው የሚባለውን ጥላቻ ለማጎልበት እንደሚጠቅማቸው ያመለከቱት ኮኔል፣ በምትኩ ቻይና፥ የአፍሪካ ሀገራትን ድጋፍ ለማግኘት የምታደርገውን ጥረት እንደሚደግፍላት አብራርተዋል።

XS
SM
MD
LG