በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በሀርቡ የሰፈሩ የኦሮሚያ ክልል ተፈናቃዮች “ያለርዳታ ስምንት ወራት አለፈን” አሉ


በሀርቡ የሰፈሩ የኦሮሚያ ክልል ተፈናቃዮች “ያለርዳታ ስምንት ወራት አለፈን” አሉ
please wait

No media source currently available

0:00 0:07:27 0:00

በሀርቡ የሰፈሩ የኦሮሚያ ክልል ተፈናቃዮች “ያለርዳታ ስምንት ወራት አለፈን” አሉ

ከኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን ጊምቢ ወረዳ ቶሌ ቀበሌ ተፈናቅለው፣ በደቡብ ወሎ ዞን ሀርቡ ከተማ እና አካባቢዋ መስፈራቸውን የሚናገሩት ሦስት ሺሕ የሚደርሱ ተፈናቃዮች፣ ምንም ዐይነት ሰብአዊ ድጋፍ ሳያገኙ፣ ስምንት ወራት እንዳለፋቸው ገለጹ፡፡

በዚኽም ሳቢያ በአጋጠማቸው የምግብ አቅርቦት እጥረት፣ አዛውንቶች ወደ ጎዳና ወጥተው ለመለመን፣ ከ200 በላይ ሕፃናት መደበኛ ትምህርታቸውን ለማቋረጥ መገደዳቸውን ተፈናቃዮቹ አስታውቀዋል፡፡ ችግራችንን ለሚመለከተው መንግሥታዊ አካል ቢያሳውቁም፣ መፍትሔ አለማግኘታቸውን አክለው ተናግረዋል።

በሀርቡ ከተማ ከሚገኙ ተፈናቃዮች አንዷ፣ የ75 ዓመቷ አዛውንት ወ/ሮ ዘሙ ዓሊ ናቸው፡፡ ወ/ሮ ዘሙ፥ የልጃቸው ልጅ እና የልጃቸው ባል ተፈጸመባቸው ባሉት ጥቃት መገደላቸውንና ጧሪ በማጣታቸውም ችግር ላይ መውደቃቸውን ይገልጻሉ። የዕድሜ ባለጸጋዋ ዘሙ ዓሊ፣ የዕለት ጉርሳቸውን ለማግኘት፣ በልመና እሰከ መሠማራት መድረሳቸውን አስረድተዋል፡፡

ሌላው አስተያየት ሰጪ፣ ከጊምቢ ዞን ቶሌ ቀበሌ መምጣታቸውን የሚናገሩት የ76 ዓመቱ አዛውንት ሐሰን ይማም በበኩላቸው፣ ዕድሜያቸው በመግፋቱ፣ የቀን ሥራ መሥራት አለመቻላቸውን አመልክተዋል፡፡

ተፈናቃዮቹ፥ “ሸኔ” ሲሉ የጠሯቸውና ራሳቸውን የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት የሚሉት ኃይሎች፣ ሰኔ 11 ቀን 2014 ዓ.ም. ፈጽመውብናል ባሉት ጥቃት፣ ከኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን ጊምቢ ወረዳ ቶሌ ቀበሌ ወደ ሀርቡ ከተማ ከመጡ፣ 11 ወራት አስቆጥረዋል፡፡

በቨርጂኒያ የሚኖሩትና ራሱን የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት የሚለው ታጣቂ ቃል አቀባይ ኦዳ ተርቢ፣ ለአሜሪካ ድምፅ በተደጋጋሚ በሰጡት ቃል፣ ታጣቂዎቻቸው በመንግሥት ወታደሮች ላይ እንጂ በሰላማውያን ሰዎች ላይ ጥቃት እንደማይፈጽሙ ገልጸው የሚነሣባቸውን ክሥ ያስተባብላሉ።

ሰብአዊ ርዳታ እስከ አሁን ለተፈናቃዮቹ ያልደረሰበትን ምክንያት አስመልክቶ ምላሽ የሰጡት፣ የደቡብ ወሎ ዞን አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ተጠሪ ጽ/ቤት ሓላፊ ኢብራሂም ይመር፣ ተፈናቃዮቹ፥ መንግሥት ወደ አዘጋጃቸው መጠለያ ጣቢያዎች እስካልገቡ ድረስ፣ ምንም ዐይነት ድጋፍ እንደማያገኙና ርዳታ ለመስጠትም አዳጋች እንደኾነ አስታውቀዋል፡፡

የዘገባውን ሙሉ ክፍል ከተያያዘው የድምፅ ና ምስል ፋይል ይከታተሉ።

XS
SM
MD
LG