በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የወለንጭቲ እና ቢሾፍቱ ከተሞች ጥቃት


Map of Ethiopia
Map of Ethiopia
የወለንጭቲ እና ቢሾፍቱ ከተሞች ጥቃት
please wait

No media source currently available

0:00 0:04:35 0:00

በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ሸዋ ዞን ቢሾፍቱ እና ወለንጭቲ ከተሞች፣ በታጣቂዎች ተፈጸመ በተባለው ጥቃት፣ ሁለት ሲቪሎችን ጨምሮ ሰባት ሰዎች መገደላቸውን፣ የየአካባቢዎቹ ባለሥልጣናት አስታውቀዋል።

ከትላንት በስቲያ ግንቦት 8 ቀን 2015 ዓ.ም. ከቀኑ 11 ሰዓት ገደማ፣ የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት፣ በወለንጭቲ ከተማ በከፈተው ተኩስ፣ ሁለት ሲቪሎች መገደላቸውን፣ እንዲሁም የቆሰሉ መኖራቸውን፣ የቦሰት ወረዳ ፖሊስ መምሪያ ሓላፊ ኮማንደር ሞሐመድ የሱፍ፣ ለአሜሪካ ድምፅ ተናግረዋል።

በሌላ በኩል፣ በቢሾፍቱ ከተማ፣ ባለፈው ቅዳሜ ግንቦት 6 ቀን 2015 ዓ.ም.፣ ማንነታቸው ባልታወቁ የታጠቁ ኃይሎች ጥቃት መፈጸሙን፣ የከተማው ኮሙኒኬሽን ጽሕፈት ቤት ሓላፊ አቶ ደጀኔ ባጂሮ ገልጸዋል፡፡

በሁለቱም ከተሞች የተፈጸሙ ጥቃቶችን አስመልክቶ፣ ከኦሮሚያ ክልልም ኾነ ከፌዴራል መንግሥት አካላት፣ ዝርዝር መረጃ ለማግኘት ያደረግነው ሙከራ ለጊዜው አልተሳካም። በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ሸዋ ዞን በወለንጭቲ እና በቢሾፍቱ ከተሞች፣ በታጠቁ ኃይሎች ጥቃቶች መፈጸማቸውን፣ የየአካባቢዎቹ ባለሥልጣናት ለአሜሪካ ድምፅ ገልጸዋል።

የቦሰት ወረዳ ፖሊስ መምሪያ ኮማንደር መሐመድ ዩሱፍ ለአሜሪካ ድምፅ ሲናገሩ፣ ለጥቃቱ፣ የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊትን ተጠያቂ አድርገዋል።

‘’ሰላማውያን ሰዎች የኾኑ ሁለት ሴቶችንና አንድ ወንድን ገድለዋል። እንዲሁም፣ አንድ ወንድ እና አንዲት ሴት በጥቃቱ ቆስለዋል፡፡ ይህ የተፈጸመው፣ ሰኞ ዕለት ከሰዓት በኋላ 11 ሰዓት ገደማ ሲኾን፣ ሥፍራውም በቦሰት ወረዳ ወለንጭቲ ከተማ ውስጥ ነው። ይህን ጥቃት ያደረሱት፣ የኦሮሞ ነፃነት ታጣቂዎች ናቸው። መንግሥት ጥቃቱን ለመመከት፣ አፋጣኝ ርምጃ ወስዶ፣ ገሚሶቹን ገድሏል፤ የተማረኩ እና የፈረጠጡም አሉ። አሁን ከተማዋ ወደ መረጋጋት ተመልሳለች’’ ብለዋል።

አቶ መሐመድ፣ በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች እና በኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት መካከል የተደረገው የተኩስ ልውውጥ፣ ለሰዓታት መቆየቱን ጠቅሰው፣ የሰው እና የትራንስፖርት እንቅስቃሴዎች ተደናቅፈው እንደነበር አክለው ገልጸዋል።

በከተማዋ ያሉ የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች በወሰዱት ርምጃ፣ ታጣቂዎቹን ከከተማዋ ለማስለቀቅ መቻሉን፣ ኮማንደር መሐመድ ተናግረዋል፡፡ በተመሳሳይ መልኩ፣ በቢሾፍቱ ከተማ፣ ግንቦት 6 ቀን 2015 ዓ.ም.፣ ማንነታቸው ለጊዜው ባልታወቁ ታጣቂዎች ጥቃት መፈጸሙ ተገልጿል።

ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ ነዋሪዎች ለአሜሪካ ድምፅ ሲናገሩ፣ ቅዳሜ፣ ግንቦት በተጠቀሰው ቀነ ሌሊት ላይ፣ በቢሾፍቱ ከተማ ውስጥ፣ ለአንድ ሰዓት ያህል የዘለቀ የከባድ መሣሪያ ድምፅ ተሰምቷል። በጉዳዩ ላይ መረጃ ለማግኘት፣ ወደ ልዩ ልዩ አካላት እና ነዋሪዎች ተደጋጋሚ ሙከራ ብናደርግም፣ የሚበዙት ስለኹኔታው ለመናገር እንደማይፈልጉና ይልቁንም ስጋት እንዳለባቸው ገልጸውናል።

የከተማው ኮሙኒኬሽን ጽሕፈት ቤት ሓላፊ አቶ ደጀኔ ባጂሮ፣ ለዐዲስ ስታንዳርድ በሰጡት መረጃ፣ ጥቃቱ እኩለ ሌሊት የተፈጸመው፣ በጨለለቃ ክፍለ ከተማ ፖሊስ ጣቢያ ላይ ሲኾን፣ የፈጻሚዎቹ ማንነት አልታወቀም። በጥቃቱም፣ የፖሊስ ጣቢያውን የሚጠብቁ አራት ፖሊሶች ተገድለዋል።

እንደ ሓላፊው ገለጻ፣ የታጣቂው ቡድን ማንነት በውል ባይታወቅም፣ የጥቃቱ ዓላማ፣ በፖሊስ ጣቢያው በሕግ ቁጥጥር ሥር የዋሉ እስረኞችን ለማስለቀቅ የተደረገ ሙከራ ነው።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት፥ የተፈጠረውን ግጭት ለማርገብበታንዛኒያ በተደረገው የቅድመ ድርድር ንግግር የተደረሰበትን ስምምነት በመጣስየፌዴራል ወታደሮች ጥቃቱን ፈጽመዋል፤ ሲል ከሧል።

ታጣቂ ቡድኑ ክሡን በማጠናከር፣ የፌዴራል ወታደሮች፥ በኦሮሚያ ክልል ልዩ ልዩ አካባቢዎች፣ በተለይም በምዕራብ እና ምሥራቅ ወለጋ፣ ምሥራቅ እና ምዕራብ ሸዋ፣ አርሲ፣ ቦረና፣ ሐረርጌ እና ሆሮ ጉዱሩ ላይ ጥቃት ፈጽመዋል፤ ብሏል።

የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ዓለም አቀፍ ቃል አቀባይ ኦዳ ተርቢ፣ ለአሜሪካ ድምፅ እንደተናገሩት፣ ጥቃቶቹ፣ በሁለቱ ተነጋጋሪ ወገኖች መካከል ከተደረሰበት መግባባት ጋራ የሚቃረኑ ናቸው፤ ብለዋል።

የታንዛኒያው የመጀመሪያ ዙር ውይይት ከተካሔደ በኋላ፣ የጋራ መግባባት የተደረሰበት የንግግር ነጥብ፣ ቀውሱን መቀነስ ቅድሚያ እንዲሰጠው የሚያሳስብ ነበር። የሚያሳዝነው ግን፣ የዐቢይ መንግሥት፣ ሌላውን መንገድ መርጧል። በተቆጣጠርናቸው አካባቢዎች ሁሉ፣ ከፍተኛ ጥቃት ፈጽሟል፤ ጥቃቱም እያደር ተባብሷል።

በሁለቱም ከተሞች ስለተፈጸሙት ጥቃቶች፣ ከኦሮሚያ ክልል እና ከፌዴራል መንግሥት ባለሥልጣናት፣ እንዲሁም ከኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽንና ከኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ፣ ዝርዝር መረጃ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ለጊዜው አልተሳካም።

XS
SM
MD
LG