በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የኮሌራ ወረርሽኝ በኢትዮጵያ አራት ክልሎች ተዛመተ፤ በደቡብ ክልል 18 ሰዎችን ገደለ


የኮሌራ ወረርሽኝ በኢትዮጵያ አራት ክልሎች ተዛመተ፤ በደቡብ ክልል 18 ሰዎችን ገደለ
please wait

No media source currently available

0:00 0:04:16 0:00

የኮሌራ ወረርሽኝ በኢትዮጵያ አራት ክልሎች ተዛመተ፤ በደቡብ ክልል 18 ሰዎችን ገደለ

የኮሌራ ወረርሽኝ በኢትዮጵያ አራት ክልሎች መዛመቱን የጤና ሚኒስቴር ሲገልጽ፣ በደቡብ ክልል ልዩ ልዩ ዞኖች እና ወረዳዎች ደግሞ፣ 18 ሰዎችን ለኅልፈት መዳረጋቸውንና 919 ሰዎች በበሽታው መያዛቸውን፣ የክልሉ ጤና ቢሮ አስታውቋል።

ወረርሽኙ በበረታባቸው የክልሉ ዞኖች፣ ትላንት እና ዛሬ ክትባት መስጠት መጀመሩን፣ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዲሬክተር አቶ ማሙሽ ሑሴን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ፣ የኮሌራ ወረርሽኝ፣ በአራት ክልሎች መዛመቱን ያስታወቀው የጤና ሚኒስቴር፣ ወረርሽኙን ለመከላከል፣ ለ1 ነጥብ 5 ሚሊየን ዜጎች ክትባት እንደሚሰጥ አመልክቷል፡፡

በኢትዮጵያ አራት ክልሎች ተዛምቶ ጉዳት እያደረሰ የሚገኘው የኮሌራ ወረርሽኝ፣ በዐዲስ መልክ በተከሠተባቸው የደቡብ ክልል አምስት ዞኖች እና ሦስት ልዩ ወረዳዎች፣ ሰዎችን ለኅልፈተ ሕይወት እና ለሕመም መዳረጉን፣ የደቡብ ክልል የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታወቀ፡፡

የኢንስቲትዩቱ ዲሬክተር አቶ ማሙሽ ሑሴን፣ ለአሜሪካ ድምፅ ሲናገሩ፣ በደቡብ ክልል እንደ ዐዲስ በተስፋፋው የኮሌራ ወረርሽኝ የ18 ሰዎች ሕይወታቸው ማለፉንና 919 ሰዎች ደግሞ በበሽታው መያዛቸውን አስረድተዋል።

በክልሉ፣ ለተከታታይ አምስት ቀናት ይሰጣል የተባለውን የኮሌራ ክትባት ዘመቻ፣ ትላንት ማክሰኞ፣ ግንቦት 8 ቀን 2015 ዓ.ም.፣ በደቡብ ኦሞ ዞን ያስጀመሩት የጤና ሚኒስቴር ዴኤታ ዶ/ር ደረጀ ዱጉማ፣ ወረርሽኙ፥ በአገር አቀፍ ደረጃ በአራት ክልሎች መከሠቱን አረጋግጠዋል።

ዕድሜያቸው፣ ከአንድ ዓመት በላይ ለኾኑ 1ነጥብ5 ሚሊዮን ዜጎች፣ የኮሌራ ክትባት እንደሚሰጥ፣ ሚኒስትር ዴኤታው ማስታወቃቸውን፣ የክልሉ መንግሥት ቴሌቪዥን ጣቢያ ዘግቧል።

የክትባት ዘመቻው፣ በደቡብ ኦሞ ዞን በናፀማይ ወረዳ የተጀመረ ሲኾን፣ ወረርሽኙ በባሰባቸው በጋሞ ዞን ማላጋርዳ ወረዳም፣ በዛሬ ዕለት መሰጠት መጀመሩን፣ በጋሞ ዞን ጤና መምሪያ የጤና እና ጤና ነክ ድንገተኛ አደጋዎች ቅኝት ዳይሬክቶሬት ዲሬክተር አቶ ታረቀኝ መርዕድ ገልጸዋል።

በጋሞ ዞን፣ እስከ ትላንትናው ዕለት ድረስ፣ ከ400 በላይ የሕመምተኞች ቁጥር መመዝገቡን የጠቀሱት ዲሬክተሩ፣ ወደ ጤና ተቋም ከመድረሳቸው በፊት አምስት ሰዎች ሕይወታቸው ማለፉንና በአጠቃላይ ስምንት ሰዎች መሞታቸውን አስታውቀዋል።

በሌላ በኩል፣ ባለፈው ሳምንት፣ በቡርጂ እና በአማሮ ልዩ ወረዳዎች በተዛመተው በዚኹ የኮሌራ ወረርሽኝ፣ ሰባት ሰዎች ለኅልፈተ ሕይወት መዳረጋቸውን መዘግባችን የሚታወስ ሲኾን፣ ለወረርሽኙ ጉዳት መባባስ፣ በልዩ ወረዳዎቹ ወሳኝ መሠረተ ልማቶች ባለመዘርጋታቸው እንደኾነ፣ የአማሮ ልዩ ወረዳ ጤና ጥበቃ ጽሕፈት ቤት የበሽታ መከላከል እና ጤና ማጎልበት ዋና የሥራ ሒደት የማኅበረሰብ ተግባቦት እና የጤና ኤክስቴንሽን አስተባባሪ አቶ አክሊሉ ካሌብ አመልክተዋል።

በጋሞ ዞን ጤና መምሪያ የጤና እና ጤና ነክ ድንገተኛ አደጋዎች ቅኝት ዳይሬክቶሬት ዲሬክተር አቶ ታረቀኝ መርዕድም፣ የአቶ አክሊሉን አስተያየት ያጠናክራሉ፡፡

የኮሌራ ወረርሽኙ፣ በዐዲስ መልክ የተከሠተባቸው የደቡብ ክልል አካባቢዎች፥ የጋሞ፣ የጎፋ፣ የደቡብ ኦሞ፣ የኮንሶ እና የጌዲኦ ዞኖች፣ እንዲሁም የአሌ፣ የአማሮ እና የቡርጂ ልዩ ወረዳዎች ናቸው።

XS
SM
MD
LG