በማላዊ፣ 37 መንገደኞችን አሳፍሮ ይጓዝ የነበረ ታንኳ፣ በጉማሬ በመገልበጡ፣ የአንድ ዓመት ሕፃን ሲሞት፣ 23 ሰዎች የደረሱበት አለመታውቁን አሶሺዬትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡
ጉማሬው፣ በደቡባዊ ማላዊ በሚገኝ ወንዝ ላይ ሲጓዝ የነበረውን ታንኳ ገጭቶ በመድፈቁ አደጋው መድረሱን ዘገባው ያስረዳል፡፡ ባለሥልጣናት ትላንት ማክሰኞ እንዳስታወቁት፣ ከተረጋገጠው የሕፃኑ ሞት ሌላ፣ የገቡበት ያልታወቁት 23 ሰዎችም ሳይሞቱ እንዳልቀሩ ተናግረዋል፡፡
ከዕንጨት የተሠራው ረጅሙ ታንኳ፣ በጉማሬው ከመገጨቱ በፊት፣ ባለፈው ሰኞ፣ በማሳንጄ አውራጃ በሚገኘው ሽሬ ወንዝ ላይ፣ 37 ሰዎችን አሳፍሮ ወደ አጎራባች ሞዛምቢክ ሲጓዝ እንደነበር በዘገባው ተመልክቷል፡፡
የማላዊ ፖሊስ፣ በአካባቢው ይንቀሳቀሱ ከነበሩና ለነፍስ አድን ሥራ ጀልባዎችን ከለገሱ የዓለም ምግብ ፕሮግራም ሠራተኞች ጋራ በመተባበር፣ 13 ሰዎችን ለመታደግ መቻሉን፣ የማሳንጄ አውራጃ ፖሊስ ኮሚሽነር ዶሚንክ ምዋንዲራ ተናግረዋል፡፡
የነፍስ አድን ፍለጋው፣ 24 ሰዓት ያለፈው በመኾኑ፣ መድረሻቸው ያልታወቁት 23 ሰዎች ሳይሞቱ እንዳልቀሩ፣ የፖሊስ ቃል አቀባይ አግነስ ዛላኮማ ስጋታቸውን ገልጸዋል፡፡
የማላዊ ፕሬዚዳንት ላዛሩስ ቸክዌራ፣ የውኃ እና ንጽሕና አጠባበቅ ሚኒስትራቸውን ወደ ሥፍራው የላኩ ሲሆን፣ በአካባቢው የሚኖሩ ጉማሬዎች፣ ብዙውን ጊዜ ተመሳሳይ ችግር የሚፈጥሩ በመኾናቸው፣ ወደ ሌላ ቦታ እንዲዛወሩ የአካባቢው ባለሥልጣናት ፍላጎታቸውን ማስታወቃቸውን አሶሺዬትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡