በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በደቡብ ምሥራቅ ናይጄሪያ የአሜሪካውያን ዐጃቢዎች ጥቃት ደረሰባቸው


በናይጄሪያ የሚገኙት አናምብራ እና ኤቦኒ ግዛቶችን የሚያሳይ ካርታ
በናይጄሪያ የሚገኙት አናምብራ እና ኤቦኒ ግዛቶችን የሚያሳይ ካርታ

በደቡብ ምሥራቅ ናይጄሪያ አናምብራ በተባለው ግዛት፣ ታጣቂዎች በአንድ የአሜሪካውያን ዐጀብ ላይ በአደረሱት ጥቃት፣ ሁለት ፖሊሶች እና ሁለት የኤምባሲ ሠራተኞች ተገድለዋል፤ ሲሉ የአሜሪካ ባለሥልጣናት እና የናይጄሪያ ፖሊስ አስታውቀዋል።

በዐጀቡ ክበብ ውስጥ፣ አሜሪካውያን አልነበሩም፤ ሲል የፖሊስ ቃል አቀባይ ተናግሯል። በግዛቱ ያሉ ተገንጣዮች፣ በፖሊስ እና በመንግሥት ተቋማት ላይ የሚያደርሱትን ጥቃት መጨመራቸው ተገልጿል።

ትላንት ተፈጽሟል በተበለው ጥቃት፣ ታጣቂዎቹ ሁለት ፖሊሶችንና ሁለት የኤምባሲ ሠራተኞችን ከገደሉ በኋላ መኪኖቻቸውን አቃጥለዋል፣ ሁለት ፖሊሶችንና ሾፌራቸውንም አግተው ወስደዋል፤ ተብሏል።

በዋሽንግተን ዲሲ፣ የአሜሪካ ብሔራዊ የጸጥታ ም/ቤት ቃል አቀባይ ጃን ኪርቢ፣ ጥቃቱን አረጋግጠዋል። “አንድ የአሜሪካ ዐጀብ ጥቃት ደርሶበታል፤ ነገር ግን በውስጡ አንድም አሜሪካዊ አልነበረም፤” ሲሉ ጃን ኪርቢ ለዜና ሰዎች ተናግረዋል።
የአሜሪካው የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴርም የጥቃቱን መፈጸም አረጋግጧል።

“በናይጄሪያ የሚገኘው የአሜሪካ ልዑክ፣ ከናይጄሪያ የጸጥታ ኃይሎች ጋራ በመኾን ጉዳዩን እየመረመረ ነው፤” ሲሉ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አመልክተዋል።

በደቡብ ምሥራቅ ናይጄሪያ ለሚደርሱ ጥቃቶች፣ ባለሥልጣናት፣ “የቢያፍራ ሕዝቦች ንቅናቄ” የተባለውን ዐማፂ ቡድን ተጠያቂ ያደርጋሉ። ቡድኑ በበኩሉ፣ በአካባቢው ለተፈጠረው ሁከት ተጠያቂ እንዳልኾነ በተደጋጋሚ አስታውቋል።

XS
SM
MD
LG