ባለፈው ወር የተቀሰቀሰውን የሱዳን ትጥቃዊ ግጭት እየሸሹ፣ በኢትዮጵያ የድንበር ከተማ በመተማ በኩል ብቻ፣ ከ20ሺሕ400 በላይ ፍልሰተኞች እንደገቡና ከእነርሱም የሚበዙት ኢትዮጵያውያን እንደኾኑ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ ርዳታ ማስተባበሪያ ቢሮ(OCHA) አስታውቋል።
የዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት(IOM)፣ እስከ አሁን፣ ከሱዳን ወደ ኢትዮጵያ የገቡ የ66 ሀገራት ዜጎችን መመዝገቡንና በሁለት መዳረሻዎች ላይ ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ ገልጿል፡፡
ፍልሰተኞቹ በብዛት የሚገኙበትን መተማ ከተማን የሚያካትተው፣ የምዕራብ ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ ቢክስ ወርቄ በሰጡን አስተያየት፣ በድጋፍ አቅርቦት በኩል ያሉ እጥረቶችን ለመፍታት ከሚመለከታቸው አካላት ጋራ እየተነጋገሩ መኾኑን አብራርተዋል፡፡ የተመድ የሰብአዊ ርዳታ ማስተባበርያ ቢሮም፣ ትላንት በአወጣው ሪፖርቱ፣ ለፍልሰተኞቹ ተገቢውን ድጋፍ ለማቅረብ ለጋሽ አካላት እጃቸውን እንዲዘረጉ ተማፅኗል፡፡
ባለፉት ሁለት ሳምንታት ውስጥ፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች፣ በግጭት ከምትናጠው ሱዳን በየቀኑ እየሸሹ ወደ ኢትዮጵያ በመግባት ላይ መኾናቸውን የገለጸው የማስተባበርያ ቢሮው፣ ዋናው የፍልሰተኞች መዳረሻ በኾነው፣ በዐማራ ክልል በመተማ በኩል ብቻ፣ እስከ አሁን ከ20ሺሕ 400 በላይ ሰዎች ገብተው መመዝገባቸውን በሪፖርቱ አስፍሯል፡፡ ከእነዚኽም የሚበዙት ኢትዮጵያውያን እንደኾኑ ጠቁሟል።
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በመተከል ዞን ጉባ ወረዳ በሚገኘው አዋሳኝ ከተማ በአልማሃል በኩል ደግሞ፣ ከሚያዝያ 16 እስከ ግንቦት 12 ቀን ድረስ፣ ከ5ሺሕ300 በላይ ሰዎች ገብተዋል፤ ብሏል። በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል በሚገኘው ኩርሙክ እና የጋምቤላው ፓካግ/ቡቢይር ከተሞች፣ ሌሎቹ የፍልሰተኞች መዳረሻዎች እንደኾኑም የተመድ የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበርያ ቢሮው ሪፖርት ያመለክታል።
ዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት(IOM)፣ ከአራቱ የፍልሰተኞቹ የመግቢያ መሥመሮች መካከል፣ በሁለቱ ሥፍራዎች በመገኘት ድጋፍ እያደረገ መኾኑን፣ ለአሜሪካ ድምፅ የገለጹት የድርጅቱ የኢትዮጵያ ቃል አቀባይ ኬይ ቪራይ፣ እስከ አሁን፣ የ66 ሀገራት ዜጎች መመዝገባቸውን ተናግረዋል፡፡
“እንደ ዓለም አቀፍ የፍልሰት ድርጅቱ፣ በአሁኑ ወቅት በሁለቱ ሥፍራዎች እንገኛለን፡፡ አንዱ እስከ አሁን፣ ከ20 ሺሕ በላይ ሰዎች የገቡበት መተማ ነው፡፡ እነዚኽም፣ የ66 ሀገራት ዜጎች ናቸው፡፡” ያሉት ቃል አቀባዩዋ፤ “ብዙዎቹ ኢትዮጵያውያን ሲኾኑ፤ የሱዳን፣ የኤርትራ፣ የተርኪዬ እና የሶማልያ ዜጎች ደግሞ እንደ ቅድመ ተከተላቸው ተከታዩን ቁጥር ይይዛሉ፡፡ ሌላው የምንገኝበት ደግሞ፣ ኩርሙክ ሲኾን፣ እስከ አሁን ከ600 በላይ ፍልሰተኞችን መዝግበናል፡፡” ብለዋል።
አክለውም “በመተከል ዞን አልማሃል በኩል ደግሞ፣ ከአምስት ሺሕ በላይ ሰዎች ወደ ኢትዮጵያ ስለ መግባታቸው፣ በሥፍራው ከሚገኙ አጋሮቻችን ሪፖርት ደርሶናል፡፡ በደኅንነት ስጋት ምክንያት በቦታው መድረስ አልቻልንም።” ያሉ ሲኾን ወደዚያ መድረስ የሚችሉበት ዕድል ካለ እንደሚሔዱ ተናግረዋል።
የተመድ የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበርያ ቢሮም እንዲሁ፣ በአካባቢው ካለው የጸጥታ ችግር ጋራ በተያያዘ፣ ወደ አልማሃል የመጓዝ ገደብ በመጣሉ፣ በሥፍራው የሚገኙ ፍልሰተኞች፣ እስከ አሁን ምንም ዐይነት ድጋፍ እንዳልቀረበላቸው ገልጿል፡፡
በአንጻሩ በሌሎች ሥፍራዎች ለሚገኙ ፍልሰተኞች፥ የምግብ፣ የውኃ፣ የመጠለያ እና ሌሎች አገልግሎቶች፣ በአጋር አካላት በኩል እየቀረቡ እንደሚገኙ፣ በትላንት ሪፖርቱ የገለጸው የማስተባበርያ ቢሮው፣ ለዚኽ አገልግሎት አመቺነትም በመቶዎች የሚቆጠሩ ፍልሰተኞችንና ጥገኝነት ጠያቂዎችን፣ ከመተማ ስድስት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወደሚገኘው ማንደፍሮ ተራራ ወደተባለው ሥፍራ የማዘዋወር ሥራ እየተሠራ ነው፤ ብሏል፡፡
ከሱዳን የተፈናቀሉ ፍልሰተኞች በብዛት ከሚገኙበት ከመተማ ከተማ፣ ከ8ሺሕ500 በላይ ኢትዮጵያውያንና ከ1ሺሕ200 በላይ የሦስተኛ አገር ዜጎች፣ ወደ ዐዲስ አበባ መዘዋወራቸውንም ኦቻ ገልጿል፡፡ ይህም የመተማ ከተማን መጨናነቅ እንደሚያቃልል ጠቁሟል፡፡
አሁን፣ በሥፍራው ይገኛሉ ላላቸው ከ10 ሺሕ በላይ ፍልሰተኞች፣ በጤና ሚኒስቴር በኩል የሚሰጠውን የሕክምና አገልግሎት ጨምሮ፣ ሌሎችም መሠረታዊ አገልግሎቶች እየተሰጡ መኾናቸውን ያብራራው ኦቻ፣ ኾኖም፣ እጥረት መኖሩን አልሸሸገም፡፡ ለዚኽም፣ ከለጋሽ አካላት ተጨማሪ ድጋፍ እንደሚያስፈልግ አመልክቷል፡፡
ብዙዎቹ ፍልሰተኞች የሚገኙበትን መተማ ከተማን የሚያካትተው የምዕራብ ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ ቢክስ ወርቄ በሰጡን አስተያየት፣ ከፌዴራል ጀምሮ እስከ አካባቢው አስተዳደር፣ ልዩ ልዩ ኮሚቴዎች ተዋቅረው ፍልሰተኞችን እያስተናገዱ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡ በድጋፍ አቅርቦት በኩል ያሉ እጥረቶችን ለመፍታት፣ ከሚመለከታቸው ጋራ በመነጋገር እንደሚሠሩ አመልክተዋል፡፡
ፍልሰተኞች ከሱዳን ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡባቸው አቅጣጫዎች፣ አራት መድረሳቸውንና አጠቃላይ የፍልሰተኞች ቁጥር እየጨመረ መቀጠሉን፣ የኦቻ ሪፖርት ያመለክታል፡፡ በመተማ በኩል ግን፣ ሰሞኑን የሚገቡ ፍልሰተኞች ቁጥር መቀነስ ማሳየቱን፣ አቶ ቢክስ ወርቄ ተናግረዋል፡፡
የዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት(IOM) የኢትዮጵያ ቢሮ ቃል አቀባይ ኬይ ቪራይ ደግሞ፣ ዜጎቻቸውን ከሱዳን በማስወጣቱ ሒደት ላይ፣ ከልዩ ልዩ ሀገራት የሚቀርበው የርዳታ ጥሪ መቀነሱን ተናግረዋል፡፡
በአጎራባች ሀገራት የሚገኙ የሱዳን ፍልሰተኞችን ለመደገፍ፣ የተመድ ተቋማትን ጨምሮ የተለያዩ አጋር አካላት በጋራ ተጣምረው ለመሥራት መዘጋጀታቸውን ይፋ ያደረገው የተመድ የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበርያ ቢሮ፣ ለዚኽም 445 ሚሊዮን ዶላር ያስፈልጋል፤ ብሏል፡፡ ከዚኽም ውስጥ፣ 76ነጥብ 9 ሚሊዮን ዶላር የሚኾነው፣ በኢትዮጵያ ለስደተኞች ምላሽ ሥራ የሚያስፈልግ እንደኾነ አመልክቷል፡፡