በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የኢትዮጵያ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት እና የኢንዱስትሪ ፓርኮች ኤክስፖርት መዳከሙ ተገለጸ


የኢትዮጵያ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት እና የኢንዱስትሪ ፓርኮች ኤክስፖርት መዳከሙ ተገለጸ
please wait

No media source currently available

0:00 0:06:44 0:00

የኢትዮጵያ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት እና የኢንዱስትሪ ፓርኮች ኤክስፖርት መዳከሙ ተገለጸ። አሜሪካ ድምፅ ያነጋገራቸው የምጣኔ ሀብት ባለሞያዎች ዶ/ር አቡሌ መሐሪ እና ዶ/ር አረጋ ሹመቴ የሰጡትን አስተያየት ከተያያዘው የድምፅ ፋይል ይከታተሉ።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ሌሊሴ ነሜ፣ በቅርቡ፣ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የንግድ እና ቱሪዝም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በአቀረቡት ሪፖርት፣ የኢትዮጵያ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨትመንት ደካማ እንደኾነና አነስተኛ ውጤት ማስመዝገቡን አስታውቀዋል፡፡

የኢንቨስትመንቱ ድክመት እና የውጤቱ ማነስ ምክንያት፥ በአገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች ያጋጠመው አለመረጋጋት፣ የውጭ ምንዛሬ እጥረት እና የመሳሰሉት መኾናቸውን ኮሚሽነሯ አመልክተዋል፡፡

የአሜሪካ ድምፅ ያነጋገራቸው የምጣኔ ሀብት ባለሞያዎች ዶ/ር አቡሌ መሐሪ እና ዶ/ር አረጋ ሹመቴ በበኩላቸው፣ የችግሩ መንሥኤ፥ በኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነሯ የተጠቀሱት ብቻ ሳይኾኑ፣ የአስተዳደር ብቃት ማነስ፣ አማሳኝነት እና የብቁ ሰው ኃይል እጥረት እንደኾኑ ያስረዳሉ፡፡

ባለፉት ዘጠኝ ወራት፣ ከውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት፣ 4ነጥብ 55 ቢሊዮን ዶላር ለማግኘት ታቅዶ፣ 2ነጥብ69 ቢሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱን፣ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ሌሊሴ ነሜ፣ በቅርቡ ለሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤቱ የንግድ እና እና ቱሪዝም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ባቀረቡት ሪፖርት አስታውቀዋል።

ኮሚሽነሯ የተገኘው ገቢ ከዕቅዱ ያነሰበትን ምክንያት ለምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴ ሲያስረዱ፥ በአገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች ያጋጠመው አለመረጋጋት፣ የውጭ ምንዛሬ እጥረት፣ የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ እና የሠራተኛ እጥረት እንደኾኑ አስረድተዋል።

በኢትዮጵያ ኢንቨትመንት ይዞታ ላይ ጥናት እያካሔዱ የሚገኙት፣ በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ባለሞያዎች ማኅበር ከፍተኛ ተመራማሪ ዶ/ር አቡሌ መሐሪ፣ ዋነኛ ምክንያቶቹ፣ በኮሚሽነሯ የተዘረዘሩት ብቻ እንዳልኾኑ ይገልጻሉ።

የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ወደ አገር ውስጥ ለማምጣት፣ መሟላት የሚገባቸው ቅድመ ኹኔታዎች መኖራቸውን፣ በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ባለሞያዎች ማኅበር ተመራማሪ ዶ/ር አረጋ ሹመቴ ይናገራሉ፡፡ የውጭ ኢንቨስትመንት ማለት፣ የውጭ ምንዛሬ ማለትም እንደኾነ የሚጠቅሱት ዶ/ር አረጋ፣ ለአገር ውስጥ ፍሰቱ አልተሟሉም የሚሏቸውን ቅድመ ኹኔታዎችን አብራርተዋል፡፡

በጦርነት እና በአለመረጋጋት ምክንያት፣ መንግሥት ትኩረቱን በመሠረተ ልማት ግንባታዎች ላይ ማድረግ አለመቻሉ፣ ከቅድመ ኹኔታዎች አንዱን ማሟላት አለመቻሉን እንደሚያሳይ የምጣኔ ሀብት ተመራማሪው አመልክተዋል፡፡ የውጭ ኢንቨስትመንት ምንጭ ሊኾኑ የሚችሉ አገሮች ራሳቸው፣ ዓለም አቀፋዊ እና የአገር ውስጥ የኢኮኖሚ ችግሮች ያሉባቸው መኾኑ ሌላው ምክንያት ነው፤ ብለዋል፡፡ የውጭ ኢንቨስትመንቱን ከፍ ለማድረግ፣ ቀዳሚ እና ዋና የሚሉት ግን፣ መልካም አስተዳደር መኾኑን አመልክተዋል፡፡

የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ፣ ችግር ከኾኑት ነገሮች መካከል፣ የውጭ ምንዛሪ እጥረት አንዱ እንደኾነ በመንግሥት መገለጹን፣ ዶ/ር አቡሌ አይቀበሉትም፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት፣ ከውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት በተጨማሪ፣ በተለይ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ኤክስፖርት፣ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋራ ሲነጻጸር፣ የ24 በመቶ ቅናሽ ማሳየቱ በሪፖርቱ ቀርቧል፡፡

የሰላም ስምምነቱን ተከትሎ፣ ጉዳት የደረሰባቸውንና ሥራ ያቆሙ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ዳግም ለማስጀመር፣ በኮሚሽኑ የጥናት ሥራዎች እየተሠሩ እንደኾነ፣ መንግሥት ማስታወቁን የአገር ውስጥ ብዝኃን መገናኛዎች ዘግበዋል፡፡

XS
SM
MD
LG