“በሠው ልጅ ሕይወት ላይ የታየው ግድ የለሽነት አሳዛኝ ነው” በሚል፣ ባለፈው ዓመት በማሊ አንድ መንደር ውስጥ 500 የሚሆኑ ሰዎች ‘በአገሪቱ ጦር ኃይሎች ውስጥ ባሉ ቡድኖች’ እና በሩሲያው ቅጥር ወታደራዊ ቡድን ዋግነር ተጨፍጭፈዋል መባሉ ምርመራ እንዲደረግበት አሜሪካ ጠይቃለች፡፡
ሞውራ በተባለው መንደር ተፈጸመ የተባለው ግድያ በማሊ የሽግግር መንግስት ምርመራ እንዲደረግበት አሜሪካ ጠይቃለች፡፡
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ትናንት ዋሽንግተን ውስጥ እንዳሉት፣ ባለፈው ዓመት በሞውራ መንደር ውስጥ ተፈጽሟል በተባለው ጭፍጨፋ እና “በሰው ልጅ ሕይወት ላይ በታየው ግድ የለሽነት” አሜሪካ እጅግ ደንግጣለች ብለዋል፡፡
የሚደረገው ምርመራም “ገለልተኛ፣ የማያዳላ፣ ውጤታማ፣ ጥልቀት ያለው እና ግልጽ” መሆን አለበት ብላለች አሜሪካ።
የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ቢሮ ባለፈው ዓርብ ባወጣው መግለጫ፣ የማሊ ወታደሮች እና “ያልታወቁ ነጭ ታጣቂዎች” ለአምስት ቀናት ባደረጉት ዘመቻ 500 ሰዎችን ሳይገድሉ አልቀረም ብሏል።
አንድ የዓይን እማኝ ሲናገሩ “እስከ 20 የሚሆኑ ሰዎችን የፊጥኝ አስረው ካንበረከኩ በኋላ ረሽነዋቸዋል፣ በጣም አሰቃቂ ነበር” ብለዋል።
የሩሲያው ዋግነር ቡድን በማሊ የሚያደርገው እንቅስቃሴ አሳሳቢ ነው ሲሉ ምዕራባዊያን ላለፉት ሁለት ዓመታት ጥያቄ ሲያነሱ ቆይተዋል።
በመፈንቅለ መንግስት ስልጣን ላይ የወጣው የማሊ መንግስት እና ሩሲያ፣ የዋግነር ቡድን በአገሪቱ የሚገኘው ስልጠና ለመስጠት እንጂ፣ ቅጥር ነፍስ ገዳይ አይደለም ብለዋል።