በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በመንግሥት እና በኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት መካከል የተጀመረው ድርድር እንዲቀጥል ተጠየቀ


በመንግሥት እና በኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት መካከል የተጀመረው ድርድር እንዲቀጥል ተጠየቀ
please wait

No media source currently available

0:00 0:05:03 0:00

በመንግሥት እና በኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት መካከል የተጀመረው ድርድር እንዲቀጥል ተጠየቀ

በኦሮሚያ ክልል ሰላም እንዲሰፍን፣ መንግሥት እና የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት የጀመሩትን የቅድመ ድርድር ንግግር እንዲቀጥሉ፣ የዩናይትድ ስቴትስ የዓለም አቀፍ ልማት ኤጀንሲ በአምቦ ከተማ በአዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ የተሳተፉ የወለጋ ዞኖች ማኅበረሰብ አባላት ተወካዮች ጠየቁ።

የምሥራቅ ወለጋ አባ ገዳ አስፋው ከበደ ለአሜሪካ ድምፅ እንደተናገሩት፣በውይይት መድረኩ ላይ የተገኙት፣ የአራቱም የወለጋ ዞኖች የማኅበረሰብ ክፍል ተወካዮች፣ “በሰላም ወጥቶ በሰላም መግባትን የተመኘ ሕዝብ፣ የድርድሩን መሳካት ይሻል፤” ብለዋል፡፡

የዩናይትድ ስቴትስ የዓለም አቀፍ ልማት ኤጀንሲ የኢትዮጵያ ፕሮግራም ዴቨሎፕመንት ሓላፊ ነጋ ተስፋዬ፣ በአገር አቀፍ ደረጃ የፖለቲካ መግባባት ይኖር ዘንድ እንደሚደግፉ ጠቅሰው፣ በኦሮሚያ የሚካሔደው የሰላም ስምምነት ሒደት፣ “ለኢትዮጵያ ሰላም ግብኣት ይኾናል፤” የሚል እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል።

በሁለቱ አካላት መካከል፣ የሰላም ድርድሩ ቢሳካም ባይሳካም፣ ብሔሮች እና ብሔረሰቦች ጥሩ ግንኙነት እንዲኖራቸው እንደሚሠሩ፣ የፕሮግራም ሓላፊው አክለው አመልክተዋል።

የዩናይትድ ስቴትስ የዓለም አቀፍ ልማት ኤጀንሲ፣ ባለፈው ሳምንት ዐርብ እና ቅዳሜ፣ በአምቦ በአዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ፣ ከምሥራቅ ወለጋ ዞን የተሳተፉት አባ ገዳ አስፋው ከበደ፣ “በሰላም ዕጦት ምክንያት፣ ሕዝቡ በሰላም ወጥቶ በሰላም መግባትን አጥብቆ ይመኛል፤” ሲሉ ተናግረዋል።

በመንግሥት እና የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት መካከል የተጀመረው፣ የቅድመ ድርድር ንግግር ቀጥሎ፣ ሁለቱ ወገኖች መግባባት ላይ እንዲደርሱ፣ ሕዝቡ በጉጉት እየጠበቀው ያለው ጉዳይ ነው፤ ሲሉ፣ በአካባቢያቸው ካለው ውጥረት እና የጸጥታ መታወክ በመነሣት ያስረዳሉ።

ወይዘሮ ምስጋኔ ዋቅጅራ፣ ከሆሮ ጉዱሩ ዞን ተወክለው በውይይት መድረኩ ላይ መሳተፋቸውን በመጥቀስ፣ በመጡበት የጃርደጋ ጃርቴ ወረዳ፣ በመንግሥት እና መንግሥት “ኦነግ ሸኔ” በሚለው የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ሸማቂዎች መካከል ባለው ግጭት፣ ዐያሌ ሰዎች ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸውንና ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች መቋረጣቸውን ገልጸዋል።

በመንግሥት እና በኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት መካከል የተጀመረው የቅድመ ድርድር ንግግር ሠምሮ ጽኑ ሰላም እንዲመጣ የተመኙበትንም ምክንያት አብራርተዋል።

ከነቀምቴ ከተማ የተሳተፉት ሌላው የማኅበረሰብ ተወካይ አቶ ተፈሪ ቀጄላም በበኩላቸው፣ በሁለቱ ወገኖች መካከል በታንዛኒያ ከተጀመረው ንግግር ጎን ለጎን፣ በአምቦው ውይይት የተሳተፉ አካላትም የሚጠበቁባቸው ተግባራት መኖራቸውን ጠቁመዋል።

የዩናይትድ ስቴትስ የዓለም አቀፍ ልማት ኤጀንሲ/USAID/ በኢትዮጵያ የፕሮግራም ዴቨሎፕመንት ሓላፊ አቶ ነጋ ተስፋዬ ዳባ፣ በአገር አቀፍ ደረጃ የፖለቲካ መግባባት እንዲኖር ተቋማቸው እንደሚደግፍ ጠቅሰው፣ ለኦሮሚያ ክልል ሰላም በታንዛንያ የተጀመረው ንግግር፣ “ለኢትዮጵያ ሰላም ግብኣት እንደሚኾን” በሚከተለው መልኩ ተስፋቸውን ገልጸዋል፡፡

በአምቦው ውይይት ላይ የተሳተፉት አባ ገዳዎች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣የዩኒቨርሲቲ መምህራን፣ ሴቶች፣ ወጣቶች እና ሌሎችም የማኅበረሰብ ክፍል ተወካዮች ወደየአካባቢያቸው ሲመለሱ፣ የሰላም ሒደቱን አስመልክቶ፣ በኅብረተሰቡ መካከል መልካም ግንዛቤ እንዲፈጠር የሚወጡት ድርሻ መኖሩን የተቋሙ የፕሮግራም ሓላፊ ጠቁመዋል፡፡ በሁለቱ ወገኖች መካከል የሚደረገው ድርድር ተሳካም አልተሳካም፣ የብሔሮች እና ብሔረሰቦች መልካም ግንኙነትም ላይ መሠራት እንዳለበት አቶ ነጋ አመልክተዋል።

ኅብረተሰቡ ለሰላም ያለው ጥማት አበረታች በመኾኑ፣ የሰላም ሒደቶችን በተመለከተ፣ ድርጅታቸው ከኅብረተሰቡ ጋራ በአጋርነት መሥራቱንም እንደሚቀጥል አክለው ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት እና የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት፣ ባለፉት ሁለት ሳምንታት ውስጥ፣ በታንዛኒያ ራስ ገዝ አስተዳደር በኾነችው የዛንዚባር ደሴት ያደረጉት የቅድመ ድርድር ንግግር፣ ያለስምምነት መጠናቀቁ ይታወሳል።

XS
SM
MD
LG