በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ሶማሊያ ከ"ጅሃዳዊያን" ጋር ባደረገችው ውጊያ ቢያንስ 21 ሰዎች ተገድለዋል


ሶማሊያ ከ"ጂሃዲስቶች" ጋር ባደረገችው ውጊያ ቢያንስ 21 ሰዎች ተገድለዋል
ሶማሊያ ከ"ጂሃዲስቶች" ጋር ባደረገችው ውጊያ ቢያንስ 21 ሰዎች ተገድለዋል

የሶማሊያ ወታደራዊ ኃይል ቅዳሜ እለት ወጣ ባለው የሀገሪቱ ክፍል በእስላማዊ አክራሪ ተዋጊዎች የተሰነዘረን ጥቃት በመመከት ቢያንስ 18 የአልሸባብ ታጣቂዎችን መግደሉን አንድ ከፍተኛ የጦር ኃይል ባለስልጣን ገልጸዋል።

ከማሳጋዋይ ከተማ አቅራቢያ በተካሄደው ጦርነት ቢያንስ ሦስት የጎሳ ሽማግሌዎች እንደሆኑ የተነገረላቸው ሰላማዊ ሰዎች መሞታቸውን ጄኔራል መሀመድ አህመድ ታረዲሾ የተባሉት ባለስልጣን በስልክ ተናግረዋል።

ማሳጋዋይ በማዕከላዊ ጋልጋዱድ የጦር ሰፈር የሚገኝበት ስፍራ ነው። ዩሱፍ ሼክ የተባሉ የአካባቢው ኗሪ ለአሶሼትድ ፕሬስ እንደተናገሩት በጥቃቱ ወቅት ታጣቂዎች የጦር ሰፈሩን ከወረሩ በኃላ ፣የጦር መሳሪያዎችን ዘርፈዋል ፣ ወታደራዊ ተሽከርካሪዎችንም አቃጥለዋል።

"በማለዳው የአልሸባብ ተዋጊዎች ወታደራዊ ሰፈሩን ጨምሮ ከተማዋን ሙሉ በሙሉ መቆጣጠራቸው የመንግስት ወታደሮች ከከተማዋ ለቀው እንዲወጡ አድርጎ ነበር " ብለዋል ዩሱፍ ሼክ።

ሼክ እንዳሉት በጥቃቱ በርካታ ሰዎች ሞተዋል፣ የገቡበት ያልታወቁ ሰዎችም አሉ።

ከአልቃይዳ ጋር ግንኙነት ያለው አልሸባብ በመዲናይቱ ሞቃዲሾ የሚገኘውን የሶማሊያ ፌደራል መንግስት ይቃወማል። ቡድኑ በሀገሪቱ ጠረፍ እና ገጠራማ አካባቢዎች የነበሩ ይዞታዎቹን በቅርብ ወራት በመንግስት ታጣቂዎች ከተነጠቀ ወዲህ በወታደራዊ መንደሮች ላይ ጥቃቱን አጠናክሮ ቀጥሏል።

የአልሸባብ አባላት በአፍሪካ ቀንዷ ሀገር እስላማዊ መንግስት ለመፍጠር ለዓመታት ሲታገሉ ቆይተዋል። የአፍሪካ ህብረት ሰላም አስከባሪ ኃይሎች እና አልፎ አልፎ ዩናይትድ ስቴትስ የአየር ጥቃቶች በአልሸባብ ኢላማዎች ላይ በማድረስ ታጣቂዎቹ ለመግታት ጥረዋል።

ሶማሊያ በአስርት ዓመታት ውስጥ የከፋ ነው የተባለውን ድርቅ በመጋፈጥ ላይ ትገኛለች ።የተባበሩት መንግስታት ዋና ፀሃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ በሀገሪቱ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት “ትልቅ ዓለም አቀፍ ድጋፍ” እንዲደረግ ተማጽነዋል ።

XS
SM
MD
LG