የአውሮፖ ህብረት ከዩክሬን በሚገቡ የምግብ ምርቶች ላይ አስቸኳይ ገደብ ለመጣል እየተዘጋጀ ሲሆን አንዳንድ የምስራቅ አውሮፓ ግዛቶች፣ ከዩክሬን የሚገባው ርካሽ ምርት በገበሬዎቻቸው ላይ ተፅእኖ እያሳደረ መሆኑን በመግለፅ ከቅርብ ቀናት ወዲህ የራሳቸውን እገዳ ጥለዋል።
ባለፈው ሳምንት ብቻ ፖላንድ ሀንጋሪ፣ ስሎቫኪያ እና ቡልጋሪያ ከዩክሬን የሚገቡ እህሎች እና ሌሎች ምርቶች ላይ ገደብ በመጣል የአውሮፓ ህብረትን ህግ መጣሳቸው ተዘግቧል።
የሀገራቸው ገበያ በሰብል መሞላቱን የገለፁት የቡልጋሪያ የግብርና ሚኒስትር ያቮር ጌቼቭ፣ በቢሊዮን የሚቆጠር ዋጋ ያለው የቡልጋሪያን ምርት መሸጥ አስቸጋሪ እየሆነ በመምጣቱ፣ እርምጃ ካልተወሰደ በስተቀር ከባድ ኪሳራ እንደሚያስከትል አመልክተዋል።
በዩክሬን አዋሳኝ ሀገሮች ውስጥም አርሶ አደረሮች የተቃውሞ ሰልፍ ማካሄድ ጀምረዋል።
ከሩሲያ ወረራ በኃላ የአውሮፓ ህብረት ከዩክሬን በሚገቡ ምርቶች ላይ የሚጣሉ ቀረጦችን እና ለገበያ የሚቀርበውን መጠን ገደብ ባለፈው አመት አንስቶ የነበር ሲሆን፣ ብራስልስ አንዳንድ ሀገራት በምርቶቹ ላይ እየጣሉት ያለው ገደብ የአውሮፓ ህብረትን ህግ የሚጥስ ነው ብላለች።
በመሆኑም የአውሮፓ ህብረት ተፅእኖ በደረሰባቸው ሀገራት የሚገኙ ገበሬዎችን ለመደገፍ 109 ሚሊየን ዶላር የሚገመት የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ እና ቢያንስ እስከ ሰኔ ድረስ የዩክሬን ምርቶች ወደሀገር ውስጥ ገበያ እንዳይገቡ ገደብ ለመጣል እየተዘጋጀ ነው።
ይህ በዩክሬን ምርቶች ላይ የሚጣለው ገደብ ለዩክሬን ገበሬዎች ከሩሲያ ወረራ ላይ ተጨማሪ የሆነ ችግር እንደሚያስከትል የዩክሬን ገበሬዎች ገልፀዋል።
የዩክሬን እህል አውሮፓን ያጥለቀለቀው ከሩሲያ ወረራ በኃላ ሀገሪቱ ምርቷን በጥቁር ባህር በኩል ወደ ውጪ መላክ ባለመቻሏ ሲሆን፣ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት አደራዳሪነት መንገዱ እንዲከፈት እና ምርቷን መላክ እንድትችል ቢደረግም፣ ሩሲያ ስምምንቱ በመጪው ነሐሴ ወር ሲጠናቀቅ ድጋሚ እንደማታድስ እያስፈራራች ነው።