በእግሊዝኛው አጠራር፣ “Children Surgery International” የተባለው፣ በተፈጥሮ የሚከሠት የከንፈር እና የላንቃ መሠንጠቅ በሚያስከትለው የአካል ጉዳት ላይ የሚያተኩር፣ ዓለም አቀፍ የበጎ አድራጎት ድርጅት ነው፡፡ በአካላዊ ጉዳቱ ሳቢያ ለበረታ የሥነ ልቡና ችግር የሚዳረጉ ሕፃናትን የሕይወት መሥመር እየቀየረ ካለው የቀዶ ሕክምና አገልግሎቱ በተጨማሪ፣ ሕክምናው በሀገር ውስጥ ቀዶ ሐኪሞች ሊሰጥ የሚችልበትን መንገድ ለማሳካት ጥረት እያደረገ ነው።
ዓለም አቀፍ ገባሬ ሠናይ ድርጅቱ፣ ባሕር ዳር በሚገኘው ጥበበ ግዮን ልዩ ሆስፒታል እየተመላለሰ ነፃ የቀዶ ሕክምና አገልግሎት ሲሰጥ፣ ከመጀመሪያ ጀምሮ አብረው እንደነበሩ የሚናገሩት፣ በሆስፒታሉ የአንገት በላይ ሕክምና ልዩ ባለሞያ ዶ/ር መለሰ ገበየሁ፣ የሕክምና ቡድኑ የመጣበትን ሥራ ሲያጠናቅቅ፣ ለቀዶ ሕክምና አገልግሎት የሚውሉ ውድ የሕክምና ቀሳቁሶችን፣ በየዓመቱ በስጦታ አበርክቶ ከመሔድ ባለፈ፣ እርሳቸውን ጨምሮ በርካታ ሐኪሞችን በሞያው እያሠለጠነ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝብ 120 ሚሊየን ያህል መድረሱ በሚነገርበት ወቅት፣ በሞያው የሠለጠነው አንድ የሕክምና ባለሞያ ብቻ መኾኑ ያሳስባቸው የሕክምና ቡድኑ መሪ እና የድርጅቱ የቦርድ ዲሬክተሮች ሊቀ መንበር ዶ/ር ሲቫ ቺናድሬ፣ በኢትዮጵያ የመጀመሪያውን ከአንገት በላይ እና የፊት ቀዶ ሕክምና ፌሎሽፕ ፕሮግራም መሠረት ለመጣል፣ ከባሕር ዳር ዩኒቨርስቲ ጋራ እየተነጋገሩ እንደኾነ ተናግረዋል፡፡
ሙሉ መረጃውን ከተያያዘው ፋይል ይመልከቱ፡፡