በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ከአያት የወረደው “የኢትዮ-ደቡብ ኮሪያ ፍቅር” በፊልሞች ቀጥሏል


ከአያት የወረደው “የኢትዮ-ደቡብ ኮሪያ ፍቅር” በፊልሞች ቀጥሏል
please wait

No media source currently available

0:00 0:11:58 0:00

ከወጥ ልብ ወለድ ፊልሞች አንሥቶ፣ እንደ ኔትፍሊክስ የመሳሰሉ የፊልም ማሠራጫ አውታሮች ላይ እስከሚታዩት ተከታታይ ፊልሞች ድረስ፣ የዓለምን የፊልም ተመልካቾች ቀልብ በከፍተኛ ኹኔታ እየተቆጣጠሩ ያሉት የደቡብ ኮሪያ ፊልሞች፣ ለኢትዮጵያ ወጣቶችም ቀዳሚ የመዝናኛ ምርጫ ከኾኑ ቆይተዋል።

በተለይ፣ ባለፉት ዐሥር ዓመታት፣ ቁጥራቸው እየጨምረ የመጣው የኮሪያ ፊልም አፍቃሪ ወጣቶች፣ ቋንቋውን ከመናገር አልፈው ለከፍተኛ ትምህርት ወደ ደቡብ ኮሪያ በመጓዝ፣ ከፍተኛ የባህል ትስስር እየፈጠሩ ይገኛሉ፤ በኢትዮጵያ የጥበብ ሥራ ላይም ተጽእኖ ማሳረፍ መጀመራቸውን ባለሞያዎች ይገልጻሉ።

የ25 ዓመቷ ወጣት ሄርሞን አጥላባቸው፣ የደቡብ ኮሪያ ፊልሞችን ማየት የጀመረችው፣ ገና የ10 ዓመት ልጅ ሳለች ነው። እርሷ እና ኹለት እህቶቿ፣ ለዕድሜያቸው የሚመጥንና ከቤተሰብ ጋራ ለማየት አዝናኝ ፊልም፣ በሳተላይት ከሚሰራጩ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ላይ ሲፈልጉ፣ ኬቢኤስ በተሰኘው የደቡብ ኮሪያ ዓለም አቀፍ ጣቢያ ላይ፣ "You are my destiny" የተሰኘውን ተከታታይ ፊልም አገኙ። ከዚያን ጊዜ ወዲህ፣ “ምርጫችን በሙሉ የኮሪያ ፊልም ኾነ፤” ትላለች ሄርሞን።

በምሥራቅ እስያ የምትገኘውና በቆዳ ስፋቷ ከአፋር ክልል ጋራ የምትስተካከለው ደቡብ ኮሪያ፣ የሕዝብ ብዛቷ፣ ከኢትዮጵያ በግማሽ ያነሰ ቢኾንም፣ በፊልም እና በሙዚቃ ሥራዎቿ ግን፣ ዝነኛውን የሆሊውድ ፊልም ለመቀናቀንና የዓለምን የመዝናኛ ኢንዱስትሪ ለመቆጣጠር ችላለች። እ.አ.አ በ2020 “ፓራሳይት” የተሰኘው የደቡብ ኮሪያ ፊልም፣ በ“ምርጥ ምስል ዘርፍ” የኦስካር ሽልማት ማግኘት ከቻለ ወዲህ፣ “ሀልዩ” የተሰኘው የፊልም ኢንዱስትሪዋም ኾነ የፖፕ ሙዚቃዋ፣ የአፍሪካ ሀገራትን ጨምሮ በመላው ዓለም ተወዳጅ ኾኗል።

እንደ ብዙዎቹ የኮሪያ ፊልም አፍቃሪ ወጣቶች፣ ሄርሞን፥ በርካታ የኮሪያ ፊልሞችን ከማዘውተሯ የተነሣ ቋንቋውን እስከ መናገር ደርሳለች። አሁን ላይ፣ ቋንቋውን በሚገባ ለመናገር ቢከብዳትም፣ ያለምንም የትርጉም ርዳታ ፊልሞቹን ለመስማት እና ለመረዳት አላዳገታትም።

ሄርሞን ተማሪ በነበረችበት ወቅት፣ “የኮሪያ ፊልም አፍቃሪያን” በሚል በዐዲስ አበባ ከሚገኙ የኮሪያ ፊልም ተመልካቾች ጋራ ማኅበር መሥርተው እንደነበር ታወሳለች። ከኻያ የማይበልጡ ተማሪዎች የመሠረቱት ማኅበርም፣ ከጊዜ በኋላ በመቶዎች የሚቆጠሩ አባሎችን ማፍራት መቻሉን ገልጻለች። እስከ ዛሬ የተመለከትኋቸው የሆሊውድ ፊልሞች በጣት የሚቆጠሩ ናቸው፤ የምትለው ሄርሞን፣ የኮሪያ ፊልሞችን የምትወዳቸው፣ “ቤተሰባዊ በኾነው ይዘታቸው ነው፤” ትላለች።

ሌላዋ ያነጋገርናት፣ የኮሪያ ፊልሞች ወዳጅ ራሔል ሰሎሞን፣ ገና የሰባት ዓመት ልጅ እያለች፣ በኮሪያ ፊልሞች ፍቅር መጠመዷን ትናገራለች፡፡ አሁን፣ የኻያ አራት ዓመት ወጣት የኾነችው ራሔል ልክ እንደ ሄርሞን፣ የኮሪያ ፊልሞችን በብዛት በመመልከትና የፖፕ ሙዚቃዎችን በመስማት ክህሎቷን በማዳበሯ፣ በደቡብ ኮሪያ የሚገኘው ውጁን ዩንቨርስቲ፣ ነፃ የትምህርት እድል ለማግኘት ረድቷታል።

አብዛኞቹ የኮሪያ ድራማዎች፣ ቤተሰባዊ ይዘት አላቸው። በቤተሰብ አባላት መሀከል ያሉ ግንኙነቶችንና ማኅበራዊ ችግሮችን አብዝተው ያነሣሉ።በሚያነሧቸው ጉዳዮችም፣ ከኢትዮጵያ ባህል እና አኗኗር ጋራ ተመሳሳይነት እንዳላቸው ራሔል አስተውላለች።

ኢትዮጵያ እና ደቡብ ኮሪያ፣ ረጅም ዘመን ያስቆጠረ እና በደም የተሳሰረ ወዳጅነት አላቸው። ከ70 ዓመት በፊት፣ ሰሜን ኮሪያ በደቡብ ኮሪያ ላይ ጦርነት ስታውጅ፣ ኢትዮጵያ፥ የ“ቃኘው ሻለቃ” ጦሯ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሥር ኾኖ ደቡብ ኮሪያን እንዲያግዝ ልካለች። ጦርነቱ ካበቃ በኋላም ይኸው ሠራዊት፣ በሰላም አስከባሪነት አገልግሏል። በዚኽ ጦርነት፣ ከፍተኛ ተጋድሎ ከፈጸሙና ድል ከተቀዳጁ ኢትዮጵያውያን መካከል ደግሞ የራሔል አያት ይገኙበታል።

በአሁኑ ወቅት በደቡብ ኮሪያ፣ የፖለቲካ ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ትምህርቷን፣ በድኅረ ምረቃ ደረጃ እየተከታተለች የምትገኘው ራሔል፣ ለደቡብ ኮሪያ ያላት ፍቅር፣ በአየቻቸው ፊልሞች እና ሙዚቃዎች የተቀረጸ ይኹን እንጂ፣ አያቷ የኮሪያ ዘማች የነበሩ መኾናቸውም፣ አገሪቱ በልቧ የተለየ ቦታ እንዲኖራት ማድረጉን ትገልጻለች።

ከ18 ዓመት ልጇ ጋራ አልፎ አልፎ የኮሪያ ፊልሞችን እንደምትከታተል የምትናገረው የቴሌቪዥን ፊልሞች እና የቴአትር ደራሲ፣ ዳይሬክተር እና አዘጋጅ መዓዛ ወርቁም በራሔል አባባል ትስማማለች። የኮሪያ ፊልሞች፣ ቤተሰብ ተኮር ከኾነው ይዘታቸው በተጨማሪ፣ ታሪካቸው ፈጣን መኾኑ፣ የልጇን ጨምሮ የብዙ ወጣቶችን ቀልብ ለመግዛቱ ምክንያት እንደኾነ ታስረዳለች።

“የኮሪያ ፋውንዴሽን ለዓለም አቀፍ የባህል ልውውጥ” የተሰኘው ተቋም በአወጣው መረጃ መሠረት፣ እ.አ.አ በ2018 “ሀልዩ”፥ ለደቡብ ኮሪያ ኢኮኖሚ፣ 9ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር ከማስገኘቱም ባሻገር፣ ደቡብ ኮሪያ በዓለም ለፈጠረችው መልካም ገጽታ አስተዋፅኦ አድርጓል። መዓዛ እንደምትለው፣ ከፊልሙ በተጨማሪ፥ ሙዚቃቸው፣ ፋሽናቸው እና አጠቃላይ የመዝናኛ ኢንዱስትሪያቸው፣ አገራቸውን በማስተዋወቅ ረገድ ትልቅ ሚና እየተጫወተ ነው፡፡

የወጣቶችን ስሜት ተቆጣጥሮ የያዘው የደቡብ ኮርያው “ሀልዩ” ፊልም እና የሙዚቃ ኢንዱስትሪ፣ በሀገር ውስጥ የኪነ ጥበብ ሥራዎች ላይስ ተጽእኖ ይኖረው ይኾን? በማለት ለመዓዛ ጥያቄ አቀርቤአለኹ፡፡

ፊልሙ፣ ትልቅ ተጽእኖ እንዳለው በምላሿ የገለጸችው መዓዛ፥ ፊልሞቻችንንና ድራማዎቻችንን የምንቀርፅበትን መንገድ መቃኘት እንዳለብን ትመክራለች፡፡ ፍጥነትን ከሚጠይቀው ትውልድ ጋራ አብሮ መራመድ የሚችሉ የፈጠራ ሥራዎችን መሥራት፣ ለሀገር ውስጥ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች የተተወ የቤት ሥራ እንደኾነ ታስገነዝባለች።

አብዛኞቹ የኮሪያ ፊልም አፍቃሪያን፣ በጋራ የሚስማሙበት ሌላው ነጥብ፣ የኮሪያ ፊልሞች ከእውነታ ጋራ የተቀራረቡና ያልተጋነኑ መኾናቸውን ነው። ራሔልም፣ ለድኅረ ምረቃ ትምህርት ከሔደች በኋላ በገሃድ ያገኘቻት አገር፣ ታሪኳንና ቋንቋዋን በፊልም እየተማረች ከአደገችው ደቡብ ኮሪያ ጋራ የተራራቀች እንዳልኾነች ትገልጻለች። በተለይም፣ የንጽሕና አጠባበቃቸውን አብልጣ ታደንቃለች፡፡

ከፊልማቸው እና ከሙዚቃቸው ባሻገር፣ በዐዲስ አበባ የኮሪያ ምግብ ቤቶች ማዕድ የምትሳተፈውና በየዓመቱ በሚካሔዱ የኮሪያ ፌስቲቫሎች ላይ የምትካፈለው ሄርሞንም፣ እንደ ራሔል፣ በአካል ደቡብ ኮሪያ ተገኝታ፣ በፊልም ያየቻቸውን የተራቀቁ ቴክኖሎጂዎች፣ ታሪካዊ ቦታዎች እና መልካም ምግባሮች በገሃድ የመመልከት ተምኔት አላት።

XS
SM
MD
LG