በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ጋምቤላዋ ሴት የሕክምና ተማሪ


ጋምቤላዋ ሴት የሕክምና ተማሪ
please wait

No media source currently available

0:00 0:06:07 0:00

በምዕራብ ኢትዮጵያ፣ በጋምቤላ ክልል፣ በጋምቤላ ከተማ ተወልዳ ያደገችው አርየት ኦጁሉ ኦማድ፣ ከልጅነቷ አንሥቶ የሕይወት ዘመን ሕልሟ፣ ሐኪም መኾን ነበር። አሪየት፣ በጋምቤላ ክልል ዘንድሮ፣ ለ12ኛ ክፍል ብሔራዊ መልቀቂያ ፈተና ከተቀመጡ ተማሪዎች መሀከል፣ በክልሉ ኹለተኛ ከፍተኛ ኾኖ የተመዘገበውን 476 አጠቃላይ ነጥብ በማምጣቷ፣ ሕልሟ እውን ኾኖ፣ ከጋምቤላ ክልል ወደ ሕክምና ትምህርት ቤት ለመግባት የቻለች ሴት ተማሪ ኾናለች።

አርየት፣ የማትሪክ ውጤቷ በተቋሙ የሕክምና ትምህርት ለመጀመር ስላበቃት ብትደሰትም፣ አመርቂ እንደኾነ ያህል ግን አይሰማትም፡፡ በ11ኛ እና 12ኛ ክፍሎችን የተሻለ ትምህርት ባገኝ ኖሮ፣ የማትሪክ ውጤቴ ከዚኽም የበለጠ ይኾን ነበር፤ በማለት ትቆጫለች።

አርየት፣ ለቤተሰቦቿ የበኩር ልጅ ናት። የመንግሥት ሠራተኛ የኾኑት አባቷ እና የቤት እመቤት የኾኑት እናቷ፣ ለእርሷ እና ለሦስት ታናናሽ እህቶቿ፣ እንዲሁም ለአንድ ወንድሟ ትምህርት ቅድሚያ መስጠታቸው፣ በትምህርቷ የተሻለ ውጤት እንድታገኝ ረድቷታል። በክልሉ የሚማሩ ሌሎች በርካታ ሴት ተማሪዎች በአንጻሩ፣ በኢኮኖሚያዊ ዐቅም ማነስ እና በጎጂ ልማዶች ሳቢያ ትምህርታቸውን ከዳር ለማድረስ እንደሚቸገሩ አርየት ትገልጻለች፡፡

አርየት፣ ከቤተሰብ ድጋፍ በተጨማሪ፣ በትምህርቷ ጥሩ ውጤት እንድታመጣ የረዳት፣ የአንደኛ እና መካከለኛ ደረጃ ትምህርቷን፣ በግል ትምህርት ቤቶች መማሯ እንደኾነ ታስረዳለች። የ11ኛ እና 12ኛ ክፍሎችን ለመቀጠል ወደ መንግሥት ትምህርት ቤት ከተዛወረች በኋላ ግን፣ በግል ትምህርት ቤቶች እንዳገኘችው ዐይነት፥ “የአስተማሪዎች ክትትል እና የትምህርት ግብዓት አቅርቦት አለመኖሩ ጎድቶኛል፤” ትላለች፡፡

በኢትዮጵያ፣ የሴቶች የትምህርት ተሳትፎ አናሳ ከኾነባቸው አካባቢዎች አንዱ የጋምቤላ ክልል ነው። በተለይም፣ ወደ ኹለተኛ ደረጃ እና ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚገቡ ሴት ተማሪዎች ቁጥር እጅግ ዝቅተኛ ነው፡፡ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ እና ባህላዊ ጫናዎችን ተቋቁመው ትምህርታቸውን መቀጠል ቢችሉ እንኳ፣ በትምህርት ቤታቸው በቂ ድጋፍ እና ክትትል አያገኙም። ይህም ክልሉ፣ በሕክምና ሞያም ኾነ በሌሎች የሥራ ዘርፎች በቂ የሰው ኃይል እንዳይኖረው በማድረግ ክፍተቱን ማስፋቱን አርየት ታስገነዝባለች፡፡

አርየት፣ የሕክምና ትምህርቷ የሚወስደውን ስድስት ዓመት አጠናቅቃ ስትመረቅ፣ ከጋምቤላ ክልል የወጣች የመጀመሪያዪቱ ሴት ሐኪም ትኾናለች። በአደገችበት ማኅበረሰብ ውስጥ ባሉት ውስን የሐኪሞች ቁጥር ላይ ተደማሪ ብትኾንም፣ በሞያዋ ወገኗን በማገልገል የልጅነት ሕልሟን የምታሳካበትን የሕይወት ዘመን ጥሪ የምትጀምርበት ይኾናል፡፡

XS
SM
MD
LG