ብዛት ያላቸው የአይሁድ ሀይማኖት ተከታዮች እየሩሳሌም ያሉ የአይሁዶችም ለሙስሊሞችም ቅዱስ ስፍራዎችን በእስራኤል ፖሊሶች ታጅበው ጎበኙ፡፡
ጎብኚዎቹ በቅዱሳን ስፍራዎቹ ዙሪያ በእግራቸው እየተዘዋወሩ ፎቶግራፍም እያነሱ የጎበኙ ሲሆን አንዳንዶች ቅጥር ግቢው በር ላይ ጸሎት አድርሰዋል፡፡
በቅርብ ዐመታት መሰል ጉብኝቶች የሚያደርጉ አማንያን ቁጥር እየጨመረ ሲሆን ይህም በብዙዎች ፍልስጥዒማውያን ዘንድ አንድ ቀን እስራኤል ስፍራውን ትቆጣጠረዋለች ወይም ትከፋፈለዋለች የሚል ጥርጣሬ አሳድሯል፡፡
የእስራኤል ባለስልጣናት በበኩላቸው የአይሁድ ሀይማኖት ምዕመናን ቅዱሳን ስፍራዎቹን መጎብኘት እንዲችሉ የሚፈቅደውን ነገር ግን በሙስሊማዊ አስተዳደር ስር በሚገኘው ስፍራ ገብተው መጸለይ የሚከለክለውን ለበርካታ ዐመታት የቆየ አሰራር ለመቀየር ፍላጎት የለንም ሲሉ አስታውቀዋል፡፡
የእስራኤል ፖሊሶች የአል አክሳ መስጂድን ከወረሩበት ካለፈው ሳምንት ወዲህ በአካባቢው ውጥረቱ እየተባባሰ ሄዷል፡፡ በተደጋጋሚ በአል አክሳ መስጂድ የሌሊት ጸሎት ለማካሄድ መብት አለን ያሉ ፍልስጥዔማውያን ድንጋይ እና ርችት ይዘው ከመስጊዱ አንወጣም ያሉ ሲሆን ፖሊሶች በኃይል አስወጥተዋቸዋል፣ ብዙዎቹን አስረዋቸዋል፣ ብዙዎቹም ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ ከአሁን ቀደም እስራኤል መስጊዱ ውስጥ የሌሊት ጸሎት እንዲደረግ የምትፈቅደው በቅዱስ ራማዳን ወር የመጀመሪያ አስር ቀን ብቻ መሆኑም ተመልክቷል፡፡