በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ቤላሩስ ከሩስያ የጸጥታ ዋስትና እንደምትፈልግ ተናገረች


የሩሲያ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን እና የቤላሩስ ፕሬዝዳንት አሌክሳንደር ሉካሼንኮ በሞስኮ ከተካሄደው የሩሲያ እና ቤላሩስ ጠቅላይ ግዛት ምክርቤት ጉባዔ በፊት የነበራቸው የፎቶ ስነስርዓት - ሚያዚያ 6፣ 2023
የሩሲያ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን እና የቤላሩስ ፕሬዝዳንት አሌክሳንደር ሉካሼንኮ በሞስኮ ከተካሄደው የሩሲያ እና ቤላሩስ ጠቅላይ ግዛት ምክርቤት ጉባዔ በፊት የነበራቸው የፎቶ ስነስርዓት - ሚያዚያ 6፣ 2023

የቤላሩስ ፕሬዚደንት አእሌክሳንደር ሉካሼንኮ ሀገራቸው ከሩስያ የጸጥታ ዋስትና ማግኘት እንደምትፈልግ ተናገሩ፡፡

ሉካሼንኮ ይህን ያሉት ዛሬ ሰኞ የሩስያ የመከላከያ ሚኒስትር ሴርጌይ ይጉን ተቀብለው ባነጋገሩበት ወቅት መሆኑን የቤላሩስ መንግሥት የዜና ማሰራጫ ዘግቧል፡፡

ሉካሼንኮ ባለፈው ሳምንት ከሩሲያ ፕሬዚደንት ቪላዲሚር ፑቲን ጋር ባደረጉት ውይይት “ቤላሩስ ላይ ወረራ ቢሰነዘር ሩስያ እንደራሷ ግዛት ልትከላከል እንደሚገባ” የተወያዩበት መሆኑን መጥቀሳቸውን ዘገባው አውስቷል፡፡

ፑቲን ባለፈው ወር ታክቲካዊ ኒውክሊየር መሣሪያዎችን ወደ ቤላሩስ እንልካለን ማለታቸው ነቀፋ እንዳስከተለባቸው ይታወሳል፡፡

ሁለቱ አጋር ሀገሮች የሚያካሂዱት የጋራ ወታደራዊ ልምምድ እንጂ ዩክሬንን ለመውረር የሚደረግ ዝግጅት እንዳልሆነ አጥብቀው ሲከራከሩ ከቆዩ በኋላ ሩስያ ቤላሩስን ለወረራዋ መንደርደሪያ እንዳደረጋችት የሚታወስ ነው፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ሩስያ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ በዩክሬን ኻርኺቭ እና ዛፖሮዢዢያ ክፍለ ግዛቶች ላይ የሚሳይል፡ የሮኬት እና የመድፍ ጥቃት ማድረሷን ትናንት የዩክሬን የጦር ኅይል አስታውቋል፡፡

የሰሜን ምዕራብ ዩክሬን ኻርኺቭ ክፍለ ሀገር አገረ ገዢ ኦሌክሳንደር ፕሮኩዲን ትናንት ዕሁድ ጠዋት በሰጡት ቃል የሩስያ የጦር አውሮፕላኖች ሁለት መንደሮች ላይ ጥቃት ማድረሳቸውን ተናግረው ሆኖም በጊዜው በሰው ላይ ስለደረሰ ጉዳት ሪፖርት እንደሌላቸው ለአሶሲየትድ ፕሬስ ገልጸዋል፡፡የኻርኺቭ አገረ ገዢ በበኩላቸው ዩክሬን ባለፈው መስከረም ከሩሲያ ኃይሎች እጅ አስለቅቃ የተቆጣጠረቻት ኩፒኒያስክ የተባለች ከተማ በሩስያ መድፍ መደብደቧን ገልጸዋል፡፡

ድብደባው መቀጠሉን ትናንት የተናገሩት አገረ ገዢው የሩስያ ኃይሎች መኖሪያ አካባቢዎች ላይ ሮኬት በመተኮስ ላይ መሆናቸውን አክለው መግለጻቸውን አሶሲየትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ የዩክሬን ፕሬዚደንት ቮሎዶሚር ዜሌንስኪ በትናንቱ የኦርቶዶክስ ክርስትና የሆሳዕና በዐል ዕለት የደረሰውን የሩስያ ጥቃት አውግዘዋል።

ዜሌንስኪ በዕለታዊ የምሽት ንግግራቸው “ሽብርተኛው መንግሥት ሆሳዕናን የሚያከብረው በዚህ መልክ ነው፡፡ ሩስያ የባሰውን ከዐለም የምትገለልበትን ተግባር እየፈጸመች ናት” ብለዋል፡፡

XS
SM
MD
LG