በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በደቡብ ሱዳን የመብቶች ጥሰት ተጠያቂ ባለሥልጣናት ዝርዝር ይፋ ኾነ


የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን፣ በርካታ የደቡብ ሱዳን ባለሥልጣናት፣ በሲቪሎች ላይ ፈጽመዋል ባሉት ሠቆቃ ምክንያት፣ የወንጀል ምርመራ ሊደረግባቸው ይገባል፤ ሲሉ ስም ዝርዝራቸውን ይፋ አድርገዋል፡፡

በደቡብ ሱዳን ጉዳይ ላይ የተቋቋመው የመንግሥታቱ ድርጅት፣ የደቡብ ሱዳን ከፍተኛ የመንግሥት እና ወታደራዊ ባለሥልጣናት፥ ለበርካታ ግድያዎች፣ አስገድዶ መድፈር እና የጾታ ባርነት ተጠያቂ ናቸው፤ ብሏል፡፡

ለአንድ ዓመት ያህል፣ በደቡብ ሱዳን በሚገኙ ስድስት ግዛቶች ውስጥ ምርመራ ሲያደርግ የሰነበተው ኮሚሽኑ፣ “በስም ከተዘረዘሩት ባለሥልጣናት አንዳቸውም ለተፈጸመው ወንጀል ተጠያቂ አልተደረጉም፤” ብሏል፡፡

“የምርመራ ግኝታችን እንዳሳየው፥ ባለፉት ዓመታት፣ ለከፍተኛ ወንጀሎች ተጠያቂ ካለመኾን የተነሣ፣ በደቡብ ሱዳን ሁከቱ ተስፋፋቷል፤ ሲቪሎች ለሥቅየት ተዳርገዋል፤” ብለዋል - የኮሚሽኑ ሊቀ መንበር ያሲም ሱካ፡፡

በደቡብ ሱዳን፣ የሰላም ስምምነት ከተፈረመበት አምስት ዓመታት ቀደም ብሎ፣ ወደ 400ሺሕ የሚጠጉ ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል፡፡

በአፍሪካ ኅብረት ይመራል የተባለውና ጥፋተኞችን ለፍርድ ያቀርባል የተባለው የፍርድ ችሎት፣ እስከ አሁን አለመመሥረቱን፣ ኤኤፍፒ በዘገባው አመልክቷል፡፡

XS
SM
MD
LG